በአማራ ክልል ከሚሴ ከተማ 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከሚሴ ከተማ 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እየተከበረ ነው

ከሚሴ ኢዜአ ህዳር 11/2015 በአማራ ክልል 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በክልሉ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በክልል ደረጃ እየተከበረ ነው።
''ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን'' በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ባለው በዓልም አፈ-ጉባኤዎች፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የተለያዩ የባህል ቡድኖችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
.jpg)
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ መሃመድ ያህያ እንደገለፁት በዓሉ በየዓመቱ በድምቀት መከበሩ የእርስ በእርስ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው።
እንዲሁም አንድነታችንንና ሰላማችንን በማስጠበቅ ቱባ ባህልና እሴቶቻችንን ለትውልዱ በማስተላለፍ የኢትዮጵያን ድንቅ ባህልና እሴት ለማስቀጠል የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን ጠቁመው፤ በክልሉ የሚገኙ ዞኖችም የየአካባቢያቸውን ባህል ለታዳሚዎቹ ያቀርባሉ፣ የልምድ ልውውጥም ይደረጋል ብለዋል።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል፣ ወግና ልማድ የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ፣የተለያዩ ክልሎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችና ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችም መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።