የ22ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በወንዶች አትሌት አቤ ጋሻው በሴቶች ደግሞ አትሌት ትግስት ከተማ አሸነፉ

261

አዲስ አበባ ህዳር 11 ቀን 2015(ኢዜአ) በ22ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በወንዶች አትሌት አቤ ጋሻው በሴቶች ደግሞ አትሌት ትግስት ከተማ አሸናፊ ሆኑ።

በ22ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በወንዶች ዘርፍ አትሌት አቤ ጋሻው ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቋል።

10 ኪ.ሜ በሚሸፍነው የታላቁ ሩጫ ውድድር ወንዶች ዘርፍ የአማራ ማረሚያ ቤቱ አትሌት አቤ ጋሻው በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ አትሌት ኃይለማርያም አማረ ከፌዴራል ማረሚያ 2ኛ እንዲሁም አትሌት ገመቹ ዲዳ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

በሴቶች ዘርፍም እንዲሁ አትሌት ትግስት ከተማ ከኦሮሚያ ደንና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።

አትሌት መስታወት ፍቅር ከአዲስ አበባ ፖሊስ በሁለተኝነት እንዲሁም ፎቴን ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሶስተኝነት ውድድራቸውን በአሸናፊነት አጠናቀዋል።

40 ሺህ ተሳታፊዎችን ያስተናገደው ታላቁ ቁጫ በኢትዮጵያ ውድድር 10 ኪሎ ሜትር ርቀትን የሚሸፍን ሲሆን መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ እየተካሄደ ይገሻል።

በእሩጫው የማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳኅለወርቅ ዘውዴ፣ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች፣ ታዋቂ አትሌቶች እና የሩጫው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በማስጀመሪያው ላይ አርቲስት ሀመልማል አበተ ከፌዴራል ማርሽ ቡድን ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር በማዘመር አስጀምረዋል።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዓለም ከሚከናወኑ የጎዳና ላይ ታላላቅ ውድድርች መካከል ከአፍሪካ በአንደኝነት በዓለም አቅፍ ደግሞ በስድስተኝነት የሚጠቅስ ውድድር ነው።

በውድድር ላይ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር የተለያዩ ሀገራት ዜጎች እና አትሌቶች በእንግድነትና በተወዳዳሪነት እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

በዚህም ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ በክብር እንግድነት እንዲሁም ሁለት የዩጋንዳ አትሌቶች ደግሞ በተወዳዳሪነት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በርካቶች ከሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር ቀደም ብሎም የአካል ጉዳተኞች ውድድር ተካሂዷል፡

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1994 ዓ.ም ተጀምሮ እስካሁን የቀጠለ የውድድር ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም መስህብ ወደ መሆን እየተሸጋገረ የመጣ ታላቅ መድረክ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም