ቀጥታ፡

ለፀረ-ሙስና ትግሉ መሳካት የበኩላችንን እንወጣለን - የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ መንግስት የያዘውን አቋም በመደገፍ ለፀረ-ሙስና ትግሉ መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ሌብነትን ለመቀነስና  ለማጋለጥ ራሱን የቻለ የአገልግሎት ቢሮ ተቋቁሞ እየሰራ በመሆኑ መረጃና ሰነድ በማቀበል ሌቦችን ለማጋለጥ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲተባበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይህንን በማስመልከት በአርባ ምንጭ ከተማ ኢዜአ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ መኮንን አሰፋ ፤ በአካባቢያቸው ከሙስና ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ፍትሃዊ አገልግሎት ለማግኘት መቸገሩን ገልጸዋል ።

መንግስት ችግሩን ለመቀነስ ቀደም ብሎ በየደረጃው የፀረ-ሙስና ተቋም ቢቋቋምም መሠረታዊ ለውጥ አለመምጣቱን አስታውሰው፤ ሌብነት ህዝብን ለመልካም አስተዳር ችግር ከመዳረግም በላይ የሀገርን  ዕድገት የሚያቀጭጭ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን  መንግስት ቁርጠኛ ሆኖ ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ ተቋማትን በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴው ብቻውን ችግሩን መፍታት ስለማይችል መንግስትና ህዝብ እጅና ጓንት በመሆን ልንሰራ ይገባል ያለው አስተያየት ሰጪው፤ ለፀረ-ሙስና ትግሉ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

 ሌብነትና ብልሹ አሰራር  በወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ ያለውን ተስፋ ጭምር እንዲጨልም እያደረገ ነው ያሉት  ደግሞ አቶ ታከለ ምትኩ ናቸው ።

በተለይ በከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሬት አስተዳደር ዘርፍ በኩል የሚፈጸመው ምዝበራ ነዋሪውን ለመልካም አስተዳደር ችግር መዳረጉን ጠቅሰዋል።

ችግሩ ከመንግስት ሹማምንቶች ጋር በመመሳጠር ነዋሪውን ከይዞታው እያፈናቀለ በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

መንግስት ሙስናን ለመዋጋት የያዘው አቋም እንደሚደግፉ ገልጸው፤ መረጃ በመስጠት ብሔራዊ ኮሚቴውን በማገዝ የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ሌላው የከተማዋ  ነዋሪው አቶ ደበበ ገዛኸኝ፤ ሙስና በፈጸሙ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ አለመወሰዱ በተለይም በመንግስት ተቋማት የሚስተዋለው ችግር እንዲያይል ዋንኛ ምክንያት ነው ብለዋል።

በዚህም  ሰዎች  ከድህነት ለመላቀቅ ከመስራት ይልቅ አቋራጭ መንገድን እንዲመርጡ በማድረግ የስራ መነሳሳትን በመጉዳት ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ከጦርነት ባልተናነስ  በሌብነት ላይ በመዝመት ስር ነቀል ለውጥ ማሳየት እንዳለበትና እሳቸውም መንግስት በመደገፍ  የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ከህዝብ ምንም አይደበቅም ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ አገልግሎት ለማግኘት ጉቦ የሚጠይቁትን አካላት በማጋለጥና በተግባሩ ባለመሳተፍ  እንደሚያግዙ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም