ቀጥታ፡

ዲፕሎማቶች አገራዊ ፍቅርን በማስቀደም ኢትዮጵያን ማገልገል ይገባቸዋል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 10 /2015 ዲፕሎማቶች አገራዊ ፍቅርን በማስቀደም ኢትዮጵያን ማገልገል እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ለዲፕሎማቶች የሚሰጠው ስልጠና እንደቀጠለ ነው።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአካዳሚው በመገኘት ስልጠና እየወሰዱ ለሚገኙ የመካከለኛ እና ነባር ዲፕሎማቶች ያላቸውን ተሞክሮና ልምድ አካፍለዋል።

ለዲፕሎማሲ ስራ ታታሪነት ቁልፍ በመሆኑ በማንኛውም ሁኔታ ጤናማ እና ገንቢ ግንኙነት መመስረት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዲፕሎማቶች አገራዊ ፍቅርን በማስቀደም ኢትዮጵያን ማገልገል እንደሚገባቸውና አካታች የስራ ባህሎችን በመለማመድ ሴቶችን በመስኩ ማብቃት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቂ የሰው ኃይል እና ተገቢ መዋቅር በማጠናከር የዲፕሎማሲ መርሕን በመከተል የኢትዮጵያን አገራዊ ጥቅም ማሳካት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የመማማሪያ መድረክና መለስተኛ የስልጠና እቅድ በማውጣት ዲፕሎማቶች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ያላቸውን ተሞክሮና ልምድ ያካፈሉ ሲሆን ለዲፕሎማሲ ስራ ራስን ማዘጋጀትና ለተግባሩ የሚያስፈልጉ ዘዴዎችን መያዝ ቁልፍ መሆኑን አስረድተዋል።

የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያን ማገልገል እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመውሰድ በርትቶ በመስራት ሀገር እና ሕዝብን ማገልገል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም