የመስቀል በዓል ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውንና ፍቅራቸውን ለዓለም የሚያሳዩበት ነው- ኢንጅነር ታከለ ኡማ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውንና ፍቅራቸውን ለዓለም የሚያሳዩበት ነው- ኢንጅነር ታከለ ኡማ
መስከረም 16/2011 የመስቀል በዓል ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውንና ፍቅራቸውን ለዓለም የሚያሳዩበት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የመስቀል ደመራ በዓል ስነ ስርዓት ላይ ተገኘተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባው “አባቶች እንደሚያስተምሩን ከመስቀል ደመራ በዓል ፍቅርን ይቅርታንና አንድነትን እንማርበታለን” ነው ያሉት። የረዥም ዘመን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ ታሪክ፣ ወግና ስርዓት እንዳለን፣ ከራሳችን አልፎ ሌሎች የሚመሰክሩት ጸጋ ያለን ኩሩ ህዝቦች መሆናችንን ለዓለም ከሚያሳዩት ክብረ በዓለላት አንዱ ደመራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መተባበርና መደመር ኃይል እንዳለው ከቀደምት አባቶቻችን ትምህርት መወሰድ እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡ “ከአንድ እንጨት ይልቅ የበርካታ እንጨቶች ችቦ ሆነው በአንድ ላይ መብራት ከፍተኛ ድምቀት እንደሚሰጥ ሁሉ እኛ ኢትዮጵያውያንም በጥቃቅን ልዩነቶች ሳንነጣጠል አንድነታችንን ማጠናከር አለብን” ብለዋል፡፡ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነትና ጠባብነትን አስወግደን ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት፣ ማሕበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና የበለጸገች ሀገርን ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው እንደሚያስቧት አይደለችም፤ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች ሀገር ናት፤ ህዝቦቿም በመካከላቸው በሚፈጠሩ ትናንሽ ችግሮች የሚለያዩ ሳይሆኑ አንድነታቸው የጠነከረና ዓለምም የመሰከረው ነው” በማለት ገልፀዋል፡፡ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እንሰራለን ብለዋል፡፡ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያጠናክርና በጎ ገጽታ ለዓለም ደምቆ እንዲታይ ማድረግም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡