ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው

ሠመራ፤ ህዳር 10/2015(ኢዜአ) ፌዴሬሽኑ ተፎካካሪ አትሌቶችን በአለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች በማሳተፍ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ገለጸች።

26ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ተጀምሯል።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የፌዴሬሽኑ  ፕሬዚደንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ፤ የአትሌቲክስ ስፖርት  የኢኮኖሚ ልማቱን በማገዝ  የማይናቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጻለች።

ተፎካካሪ ስፖርተኞችን  በአለም አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች እንዲሳተፉ በማመቻቸት የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባት ላይ ፌዴሬሽኑ  ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግራለች።

በተጨማሪም በጀት ዓመቱ  ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና ትብብር መስራት በመቻሉ ስኬታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም የበኩላቸው ገንቢ ሚና ለተወጡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ሁመድ በበኩላቸው፤ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በማጉላት የማይተካ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

ይህ የበለጠ ተጠናክሮና ጎሎብቶ እንዲቀጥል ክልሉ እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

የፌዴሬሽኑ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም በሠመራ ከተማ መካሄዱ ተቀራርቦ ለመስራት ከሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ በተጨማሪ በክልሉ ስፖርቱ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይ የሁሉም ክልሎች የዘርፉ ተወካዮችና ክለቦች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን፤ የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የተያዘው የስራ ዘመን  እቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም