የባንክ ዘርፉ የሪፎርም ስራዎች የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ጨምሯል - ኢዜአ አማርኛ
የባንክ ዘርፉ የሪፎርም ስራዎች የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ጨምሯል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 በባንክ ዘርፍ ላይ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ ባንክ ከግንቦት 11 ቀን 2012 ጀምሮ ከባንኮች በጥሬ ገንዘብ ወጪ የሚደረግ ብር ላይ ገደብ የሚጥል መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።
በዚህም በግለሰብ ደረጃ በቀን እስከ 200 ሺህ ብር፣ በወር ደግሞ እስከ 1 ሚሊዮን ብር፣ በኩባንያ ደረጃ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር፣ በወር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ብቻ ማውጣት እንደሚቻል መገለጹም እንዲሁ ።
ከዚህም በተጨማሪ ክፍያዎችን መፈጸም የሚቻለው ከአካውንት ወደ አካውንት፣ በቼክና በሲፒኦ እንዲሁም በሌሎች በኤሌክትሮኒክስ አማራጮች ብቻ መሆኑም ተመላክቷል።
ባንኮችም ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ ከፍለው ሲገኙ የልዩነቱን 25 በመቶ ቅጣት እንደሚከፍሉ የብሔራዊ ባንክ የደነገገው መመሪያ ያሳያል።
ከባንኮች በጥሬ ገንዘብ ወጪ የሚደረግ ብር ላይ ገደብ የሚጥለው መመሪያ ወንጀሎችን ለመከላከልና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቀነስ አንዲሁም ዓለም አቀፍ የዲጂታል ሽግግር ለማሳለጥ ያለመ ነው ።
በተጨማሪም በፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ግልጽነትና ውጤታማነትን ከማስፈን፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ፣ የፋይናንስ አካታችነትና ሁሉን አቀፍ እድገት ከማምጣት አኳያ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ለኢዜአ እንዳሉት በባንክ ዘርፍ ከተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች መካከል የጥሬ ገንዘብ ገደብ ተጠቃሽ ነው፡፡
በተወሰደው የማሻሻያ እርምጃም የጥሬ ገንዘብ ሚና እየቀዘቀዘ እንዲመጣ እንዲሁም ብዙ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶበት የሚታተመውን የገንዘብ ኖት ጉዳት እንዳይደርስበት አግዟል ብለዋል።
መመሪያው ህብረተሰቡ ወደ ዲጂታል የባንኪንግ ስርዓት እንዲገባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አብራርተዋል።
በአገሪቱ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ በተወሰደው እርምጃ በሞባይል ባንኪንግ ብዙ ገንዘብ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 52 ሚሊዮን ደርሷል ብለዋል።
አሁን ላይ በርካታ የዲጂታል ባንኪንግ አማራጮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን እነዚህም የህብረሰቡን የዲጂታል ባንኪንግ አጠቃቀም በማሳደግ ረገድ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝተዋል ብለዋል።
ይህም የባንክ ተጠቃሚው ከጥሬ ገንዘብ ጋር ያለውን ንክኪ መቀነስ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የብር ኖት ቅያሪን ተከትሎ በርካታ ደንበኞች ወደ ባንክ ስርዓት መምጣታቸውን ገልጸው አሁን ላይ ከ 100 ሚሊዮን በላይ የባንክ ሂሳብ መኖሩንም ተናግረዋል።
እንዲሁም ባንኮች አሁን ላይ ያላቸው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 1 ነጥብ 84 ትሪሊዮን መድረሱን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።