ኢትዮጵያ በገንዘብ የሚደገፍ ሽብርተኝነትን ለመከላከል በቁርጠኝነት ትሰራለች…የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በገንዘብ የሚደገፍ ሽብርተኝነትን ለመከላከል በቁርጠኝነት ትሰራለች…የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም
ህዳር 10 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ሽብርተኝነትን እና አለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖችን በመዋጋት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ ።
በሚኒስትሩ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በኒው ዴሊ፣ ህንድ እየተካሄደ ባለው 3ኛው የፀረ ሽብር ፋይናንስ የሚኒስትሮች ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ።
“ለሽብር የሚውል ገንዘብ የለም '' በሚል መሪ ሃሳብ ከህዳር 9 ቀን ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እየተካሄደ ባለው በዚህ ኮንፈረንስ ላይ አቶ ብናልፍ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት ሽብርተኝነትን እና አለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖችን በመዋጋት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እየሰራ ይገኛል።
በአለም አቀፍ እና በሀገር ደረጃ የሚደረጉ የሽብር ተግባራትን በመከላከል ህገወጥ የፋይናንስ ግብይቶችንና የገንዘብ ዝውውርን ለመዋጋት የመንግስት ተቋማትና የፋይናንስ መረጃ ማዕከላት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አስረድተዋል።
ሽብርተኝነት ዓለም አቀፍ ስጋት መሆኑን በመረዳት ተቋማዊ ሥርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ ብናልፍ ኢትዮጵያ በገንዘብ የሚደገፍ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል ።
የሰላም ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከሕንድ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሚት ሻህ ጋር የአገራቱን የሁለትዮሽና የባለብዙ መድረክ ግንኙነት የጋራ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ማጠናከር በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
ሶስተኛው የሚኒስትሮች የፀረ-ሽብር ፋይናንስ ጉባኤ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ የሰላም ሚኒስትር በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ዋቢ በማድረግ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።