የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለኢትዮጵያ ያመጣል - የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለኢትዮጵያ ያመጣል - የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለኢትዮጵያ እንደሚያመጣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለጸ።
ኢትዮጵያ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ከፈረሙ የአፍሪካ አገራት አንዷ መሆኗ ይታወሳል።
ነፃ የንግድ ቀጣናን ማቋቋም የሚያስችል ጥናትና ልዩ ልዩ ዝግጅት ሲደረግ ከቆየ በኋላም በቅርቡም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የድሬደዋ ከተማ ነፃ የንግድ ቀጣናን በይፋ ስራ አስጀምረዋል።።
በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን ጽህፈት ቤት የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ኃላፊው አቶ ተስመገን ይሁኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በድሬዳዋ ከተማ ተግባራዊ ያደረገችው ነፃ የንግድ ቀጣና ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን የሚያመጣ ነው።
በርካታ የዓለም አገራት ነፃ የንግድ ቀጣና አቋቁመው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እንደ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ እና ሱማሌ ላንድ ያሉ ጎረቤት አገራት የኢትዮጵያን ገበያ ታሳቢ ያደረገ ነፃ ንግድ ቀጣና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ነፃ ንግድ ቀጣና መኖሩም የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የውጭ ንግድን በማነቃቃት እና በሥራ ዕድል ፈጣራ ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው እድሎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በነፃ ንግድ ቀጣናው የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የበለጠ ለማሳደግ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ ፖሊሲውም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል ብለዋል።
የነፃ ንግድ ቀጣና ፖሊሲውም የአሰራር ስርዓቱን በተሻለ መልኩ በማሳደግ አገልግሎቱን የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ፖሊሲውም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመለየት የሚፈቱበትን፣ ኃላፊነትን በሚገባ ለመወጣት እና የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር በግልጽ እንዳስቀመጠ አንስተዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣና ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል መመርያ እና የህግ ማዕቀፍ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ነፃ የንግድ ቀጣና ስርዓቱ ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑ ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው ለሚገቡ ባለኃብቶች፣ ሰራተኞች እና የተቋሙ የሰው ኃይል ተከታታይ የስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሎጂስቲክስ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው በቀለ፣ ከነፃ ንግድ ቀጣናው የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ነፃ ንግድ ቀጣናው ለመሳብም የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግም ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ቱርክ፣ ቻይና፣ ታይዋን ያሉ በርካታ የዓለም አገራት ነፃ የንግድ ቀጣና ኢኮኖሚያዊ አቅጣጫን ተከትሎ ውጤታማ እንደሆኑ በመጥቀስ፤ የአገራቱን መልካም ተሞክሮ መውሰድ እንደሚጠቅምም ተናግረዋል።