ቀጥታ፡

ለሕዳሴው ግድብ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን- የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች

ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ እስኪያልቅ ድረስ ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ ለሕዳሴው ግድብ ዋንጫ አቀባበል በተዘጋጀ የገቢ አሰባሰብ መርሃግብር በአንድ ቀን ብቻ ከ15 ሚለዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋሬ ጋዳ ገልጸዋል።

የግድቡ ዋንጫ ትናንት ወደ ዞኑ መምጣትን ምክንያት በማድረግ የዞኑ ነዋሪዎች ለሕዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛትና በስጦታ ድጋፉ እያደረጉ ይገኛሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል በዞኑ የአባያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገዛሀኝ በሬሳ ግድቡ የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ የጥንካሬ እና የጽናት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገር ስትለማና ስታድግ የዜጎች ህይወት ይለወጣል ያሉት አርሶ አደሩ፣ የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ወደ ዞኑ መምጣትን ምክንያት በማድረግ የ30 ሺህ ብር የቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ከራሳቸው በተጨማሪ በአካባቢያቸው ህብረተሰቡን በመቀስቀስ በቦንድ ግዥ እንዲሳተፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

"የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ወደ ዞናችን መምጣት የልማት ተሳትፏችንን ለማጠናከር እድል ይሰጠናል" ያሉት ደግሞ የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፋኖሴ ግርማ ናቸው።

ኢትዮጵያ ከችግሮች ወጥታ የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ ሙሉ ትኩረትን እንደ ሕዳሴው ግድብ ላሉ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ትናንት በተካሄደ የገቢ አሰባሰብ መርሀግብር የወር ደመወዛቸውን ለሕዳሴው ግድብ በመስጠት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አመልክተዋል።

የአባያ ወረዳ ነዋሪ አቶ ማሪያም ቶሮ በበኩላቸው "የሕዳሴው ግድብ ከተባበርን የልማትም ጀግኖች መሆናችንን ለዓለም ጭምር የምናረጋግጥበት አርማችን ነው" ብለዋል።

የዋንጫውን መምጣት ምክንያት በማድረግ የ23 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው፣ በሁሉም የልማት ሥራዎች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

"የወረዳው ህዝብ የዓባይ ግድብ ልማት ብቻ ሳይሆን የአንድነታችንና የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭ መሆኑን ተገንዝቦ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል" ያሉት ደግሞ የአባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ቱሬ ናቸው።

የግድቡ ዋንጫ መምጣትን ምክንያት በማድረግ ከወረዳው በአንድ ቀን 1 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ይህም ህዝቡ ለልማት ያለውን ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋሬ ጋዳ በበኩላቸው፣ የዞኑ ህዝብና አስተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫን ተቀብሎ ገቢ የማሰባሰብ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የዋንጫውን አቀባበል አስመልክቶ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ከዞኑ ህዝብ በአንድ ቀን ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በቦንድና በስጦታ ለመሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ እያሳዩ ያለው ተሳትፎ ለልማት አጀንዳዎች ጽኑ አቋም እንዳላቸው የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም