በጋምቤላ ክልል 17 ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል 17 ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀምሯል
ጋምቤላ (ኢዜአ) ህዳር 10/2015 በጋምቤላ ክልል 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር መጀመሩን የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።
የክልሉ ምከር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትሁት ሐዋሪያት በዓሉን በማስመልከት ዛሬ በተዘጋጀ የማስ ስፓርት ላይ ለኢዜአ እንደገለጹት "ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ በክልል ደረጃ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በዓሉ እየተከበረ ያለው "የማስ ስፖርት"ን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተሳተፉበት የፓናል ውይይት፣ በተማሪዎች ጥያቄ እና መልስ ውድድርና በሌሎች ዝግጅቶች መሆኑንም አስታውቀዋል።
ምክትል አፈጉባኤዋ እንዳሉት በዓሉ በክልል ደረጃ እየተከበረ ያለው በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት ነው።
በዓሉ በመጪው ህዳር 20 ቀን 2015 ዓ.ም በጋምቤላ ስቴዲዮም የህዝቦችን አንድነትና ባህላዊ እሴቶች በሚያጠናክር መልኩ ተከብሮ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል።
በደረጃው እየተካሄደ ባለው የፓናል ውይይትም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆኑን ወይዘሮ ትሁት ገልጸዋል።
በየመድረኩም በፌዴራል ስርዓት ምንነት፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጽሁፎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት እየተደረገባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።