የላፕሴት ኮሪደር ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ዕድል ይዞ የመጣ ነው - የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን

194

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው የ"ላፕሴት ፕሮጀክት" የኢትዮጵያ ተጨማሪ ዕድል ይዞላት መምጣቱን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ገለጸ።

የላፕሴት ፕሮጀክት በፍጥነት መንገድ፣ ባቡርና ሌሎች ግዙፍ መሰረተ ልማቶች አማካኝነት ሶስቱን አገራት የማቆራኘት አላማን ያነገበ ነው።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የላሙ ወደብ የመጀመሪያው የመርከብ ማቆያ በወቅቱ የኬንያ ፕሬዚዳንት በነበሩት ኡሁሩ ኬንያታ ግንቦት 2013 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን የሎጅስቲከስ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ አቶ ያለው ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ በተለይ ለኢትዮጵያ አማራጭ ዕድል ይዞ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በማቋቋም ጭምር ቀጣናው በኢኮኖሚ እንዲተሳሰር ሚናዋን እየተወጣች መሆኗን ጠቅሰው፤ በቅርቡ የተመረቀውን የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአጀንዳ 2063 የተያዙ የአፍሪካ ውጥኖችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለቀጣናዊ ትስስር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

አጀንዳ 2063 አፍሪካን በኢኮኖሚና ፖለቲካ ዘርፍ ኃያል የማድረግ ግብ መያዙን አስታውሰው፤  ከዚህ አኳያ የላሙ ኮሪደር የቀጣናውን አገራትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነት ለማጎለበት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ በኩል ያላት የሎጅስቲክስ እንቅስቃሴ እየጨመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አማራጭ ኮሪደር እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ የላሙ ኮሪደር የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ አማራጭ የሎጅስቲክስ ኮሪደር እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡

የንግድ ኮሪደሮች እና መንገድን ጨምሮ የመሰረተ ልማት መስፋፋት ደግሞ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በላሙ ኮሪደር አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ የግብርና ምርታማነትን እያስፋፋች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኮሪደሩ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚጨምረው ተናግረዋል፡፡

በጎረቤት ሀገራት መካከል የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ያላደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የላሙ ኮሪደር የሕዝብ ለሕዝብና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር በቀጣናው የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲኖር እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

በቀጣናው ከተሞች እንዲስፋፉ የማድረግ ፋይዳ እንዳለውም በመጠቆም፡፡

አፍሪካ በአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አማካኝነት ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ንግድን ለማሳለጥና የተሻሉ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር እየሰራች ሲሆን፤ በዚህም በአህጉሪቷ የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ውጥን ተይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም