ቀጥታ፡

የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማዘመን የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማዘመን የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር እና ኢስት አፍሪካ ትሬድ ማርክ የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ናቸው።

ተቋማቱ በጋራ መስራት የሚስችላቸውን የሶስትዮሽ መግበቢያ ስምምነት ነው የተፈራረሙት።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፣ የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ዘላለም መሰለ እና የኢስት አፍሪካ ትሬድ ማርክ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታዮ ፈርመውታል።

በመግባቢያ ስምምነቱም የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር አገልግሎት አሰጣጣቸውን በዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

በስምምነቱም የተቋማቱን የኢንፎርሜሽን ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታ በማሳደግ የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታቸውን ለማዘመን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፤ ሰምምነቱ ተቋሙ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሶስቱም ተቋማት ስምምነቱን አገር አቀፍ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ ዘላለም መሰለ፤ ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የኢስት አፍሪካ ትሬድ ማርክ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታዮ፤ ስምምነቱ በዘርፍ ያለውን የግብይት ስርዓት ለማዘመን እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ለተግባራዊነቱም ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል።

የኢስት አፍሪካ ትሬድ ማርክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 የተመሰረተ ሲሆን፤ በዋናነት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የንግድ ስርዓት የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመቀነስ ምቹ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር የሚሰራ ተቋም መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም