ቀጥታ፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት እናግዛለን-የሃይማኖት አባቶች

ጋምቤላ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 በጋምቤላ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ እንደሚሰሩ የሃይማኖት አባቶች አስታወቁ።

በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች በቅድመ ግጭት መከላከልና አፈታት ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሄደዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ፓስተር ኡሞው ኡኩሪ እንዳሉት የእምነት አባቶች በሰላም ግንባታ ዙሪያ የላቀ ድርሻ አላቸው።

መንግስት በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ለጀመራቸው ስራዎች መሳካት ህዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የእምነት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ችግሮችን የመፍታት አቅም ያላቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሸህ ሙሀመድ ሀሰን ናቸው።

ፈጣሪ የሚያዘውን አስተምህሮና በወይይቱ ያገኙትን ግንዛቤ በማቀናጀት በክልሉ ያለውን ሰላም ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የታየውን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ ሌላው ፓስተር ጆን ቾል ናቸው።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ቸንኮት ቾት የክልሉ መንግስት ያቀዳጃቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት ዘላቂ ሰላም ሲኖር  ነው።

የሃይማኖት አባቶች በህዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የውይይት መድረኩ ዓላማ በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት በቅድመ ግጭት መከላከልና አፈታት ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ በሰላም ዙሪያ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ሀላፊው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም