በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 65 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል- ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 65 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል- ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አሁን ካለበት 52 ነጥብ 7 በመቶ ወደ 65 በመቶ ለማሳደግ እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ የኢትየጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄ ያለበትን ደረጃ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን ነው የተናገሩት፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪውን ማነቃቃቱን ጠቅሰው፤ በዚህም በርካታ ኢንቨስትመንት ወደ ዘርፉ መሳብና የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች እንዲያመርቱ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ንቅናቄው መጀመሩን ተከትሎ ተዘግተው የነበሩ 179 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን አንስተው አሁንም ዘርፉ ለበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተጋለጠ በመሆኑ ይበልጥ በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪው በግብዓትነት የሚውሉ ሃብቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖሩን ያነሱት ሚኒስትሩ በዘንድሮ ዓመትም በንቅናቄው የተመዘገቡ ውጤታማ አፈጻጸሞችን በማጠናከር ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ አካላት በኢትየጵያ ታምርት ንቅናቄ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ በዘንድሮው ዓመትም ንቅናቄው የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡