ቀጥታ፡

በግለሰቦች እጅ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተበረከቱለት

አዲስ አበባ ህዳር 09 ቀን 2015 (ኢዜአ) በግለሰቦች እጅ የሚገኙ አምስት ቅርሶች በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሥር ለሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በስጦታ ተበረከቱለት።

ቅርሶቹን የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርእድ ተረክበዋል።

ለተቋሙ የተበረከቱት ቅርሶች በተለያዩ ወቅቶች በግለሰብ እጅ የገቡና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ መሆናቸው ተገልጿል።

ከተበረከቱት ቅርሶች መካከል የራስ እምሩ ካባ፣ የራስ አበበ አረጋይ ሜዳልያ እና የጦር አርበኝነታቸውን የሚያትት በሶፍት ኮፒ የተዘጋጀ ዜና መዋእል ይገኙበታል።

ከፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የተበረከተ የ17ኛው ክፍለ ዘመን አዶ (የገበታ ስእል) እና በፕሮፌሰር ጀምስ ማካን የተለገሰ በ 18ኛው ክፍለ ዘመን የተለያዩ ጽሁፎችን ያካተተ ብራናም ተበርክቷል።

በተጨማሪም በሶፍት ኮፒ የተዘጋጀ ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቤተ-መጻህፍት የተገኘ ዜና መዋእል፣ የ18ኛው ክፍለ ዘመን ታሪከ ነገስትና የኢትዮጵያን የቤተ-ክህነት ሥርዓት የሚያሳይ ልዩ መጽሐፍ እንደሚገኙበትም በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።

ቅርሶቹን የተረከቡት የተቋሙ ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ መርድ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እራሱን በማሳደግ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል።

ተቋሙ በዛሬው እለት የተረከባቸው ቅርሶች በገንዘብ የማይተመኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ ስጦታውን የሰጡ አካላትን አመስግነዋል።

ቅርሶቹ በቀጣይ ለሚኖሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸውም አስረድተዋል።

በተለያዩ ግለሰቦች እጅ ታላላቅ ታሪኮችን የያዙ ቅርሶች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እነዚህን ለደህንነታቸው ሲባል ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ለሙዝየሞች በመስጠት ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ስለ ቅርሶቹ ማብራሪያ የሰጡት ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ በበኩላቸው፤ ቅርሶቹ በታሪክ ላይ ለሚሠሩ ተመራማሪዎች ትልቅ መረጃ የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በርክክቡ ማጠናቀቂያ ላይም ቅርሶቹን ላበረከቱ ግለሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም