የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ የስታትስቲክስ መረጃዎች በመደገፍ ውጤታማነቱን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ የስታትስቲክስ መረጃዎች በመደገፍ ውጤታማነቱን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ በዘመናዊ የስታትስቲክስ መረጃዎች በመደገፍ ውጤታማነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ።
የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቀን በአዲስ አበባ የተከበረ ሲሆን ዓላማውም የስታትስቲክስ መረጃ ለግብርና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያለውን ጠቀሜታ ለማስገንዘብ ነው።
አፍሪካም እንደ አህጉር የ2063 አጀንዳ ለማሳካት ያላት ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ አገራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ለማመላከትም ነው።
የስታቲስቲክስ መረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚኖረው ድርሻም ላይ ውይይት ተካሂዷል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ግብርና የኢትዮጵያ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን አንስተው በ2013/14 የምርት ዘመን ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ምርት መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉና ግብርናን ዋነኛ የኢኮኖሚያቸው መሰረት ያደረጉ አገራት የተጠናከረ የስታትስቲክስ መረጃ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ በገቢም ይሁን በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በኩል አገሪቱ የሚጠበቀውን ያህል አልተጓዘችም ነው ያሉት።
ግብርናውን ለማሳደግ የዘመነና ጥራት ያለው የስታትስቲክስ መረጃ ሊኖርና በዚህ ላይ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ነው ሚኒስትሯ አጽንኦት የሰጡት።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አቅሙን በማሳደግ መረጃ አሰባሰብ እና ትንተና ዙሪያ የሚጠቀመውን ቴክኖሎጂና አሰራር ማሳደግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት እንዲጠናከርም መንግሥት የሚያደርገውም ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ከግብርና ዘርፍ ባለፈ በአምራችና ማዕድን መስኮችም የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የሚያስችላት እቅድ አውጥታለች አቅዱ እንዲሳካ የተጠናከረ መረጃ አያያዝ ስርዓት እንደሚጠይቅም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል በግብርና እንደሌማት ትሩፋት ዓይነት ትልልቅ አገራዊ እቅዶችን ይዛለች።
እቅዱ ግቡን እንዲመታ የስታትስቲክስ መረጃን መተንተንና መጠቀም ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ጠቀሰው ቀኑ በኢትዮጵያ መከበሩም አገሪቱ ከያዘችው ግብ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ስታትስቲክስ ማዕከል ዳይሬክተር ኦሊቨር ቺንጋኒያ እንዳሉት አፍሪካ እንደ አህጉር በአጀንዳ 2063 በኢኮኖሚ የበለጸገች አፍሪካን መፍጠር እቅድ መያዙን አስታውሰው ለዕቅዱ ትግበራ የስታትስቲክ መረጃዎች በስፋት መጠቀም ይገባል።
በስታትስቲክስ የተሰበሰበው መረጃ ለፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላት ግብዓት ሊሆን የሚችል የጠራ መረጃ መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉዳት እንደደረሰበት ያነሱት ዳይሬክተሩ አፍሪካ በኢኮኖሚ እንድታገግም መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ደግሞ የስታትስቲክስ መረጃዎችን አዘምኖ መጠቀም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቀን በ1959 ዓ ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት መከበሩ ይታወሳል።