ቀጥታ፡

በምዕራብ ጉጂ ዞን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 ከምዕራብ ጉጂ ዞን ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ አባያ ወረዳ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ከ13 ወረዳዎች የተውጣጡ የነዋሪዎች ተወካዮች፣ አባ ገዳዎችና ሀደ ስንቅዎች በወረዳው በጓንጎአ ከተማ አቀባበል አድርገውለታል።

የምዕራብ ጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ዋሬ ጋዳ የዞኑ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ በሰላምና በልማት ስራዎች ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በተለይ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በየዓመቱ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

ህዝቡ ዛሬም የህዳሴ ግድብ ዋንጫው ወደ ዞኑ መምጣቱን ምክንያት በማድረግ ያለውን አውጥቶ በመስጠት ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የዞኑን ሰላም በንቃት ከመጠበቅ በተጓዳኝ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአቀባበል ስነ-ስርአቱ ላይ በቦንድ ግዥ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅና የተሰጠ ሲሆን ዋንጫው ወደ ሃምባላ ዋማና ወረዳ እንደሚሸኝ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም