ቀጥታ፡

ዶክተር አሸብር ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዕጩነት ራሳቸውን አገለሉ

አዲሳ አበባ ግንቦት 11/2010 ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት በዕጩነት ቀርበው የነበሩት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ራሳቸውን ከምርጫው አገለሉ። ከምርጫው ራሴን ለማግለል የተገደድኩት "ባለው ትርምስ ደስተኛ ስላልሆንኩ ነው" ብለዋል። በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎቱ እንዳልነበራቸው፤ ነገር ግን ከክልሉ በቀረበ ጥያቄ በዕጩነት መቅረባቸውን ተናግረዋል። ዶክተር አሸብር ዕጩ አድርጎ ውክልና የሰጣቸውን የደቡብ ክልልን ወክለው ባለመወዳደራቸው ይቅርታ ጠይቀዋል። ዶክተር አሽብር ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር በማሰብ ከቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነታቸው የለቀቁበት መንገድ ትክክለኛ አካሄድን የተከተለ አይደለም በሚል በተወሰኑ ክልሎች ቅሬታ ሲቀርብባቸው እንደነበር ይታወሳል። ለምርጫው ዝግጅት በዕጩዎቹ አቀራረብ፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች አመራረጥ ላይ በርካታ ውዝግቦችን ያስተናገደው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈጻሚዎች ምርጫ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን በፕሬዝዳንንት እየመሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም