የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አንድነታችንን የሚያጎለብትና የሚያጠናክር ነው

286

ሀረር ህዳር 09/2015 (ኢዜአ) የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን የሚያጎለብትና የሚያጠናክር ነው ሲሉ የሀረሪ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አሪፍ መሀመድ ገለፁ።

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህዳር 29 ቀን 2015ዓ.ም  በሲዳማ ክልል አዘጋጅነት ለ17ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

የክልሉ የማህበረሰብ ክፍሎችና የአጎራባች ክልሎች እንግዶችን ያሳተፈ በህገ መንግስቱ አስተምህሮት እና በህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ፅንስ ሃሳብ ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም ጠቁመዋል፡፡

በሀረሪ ክልልም በዓሉን በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በፅዳት ዘመቻ፣ ከአርሶ አደሩ ጋር ምርት በመሰብሰብ እንዲሁም በደም ልገሳ እየተከበረ እንደሚገኝም የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አሪፍ መሀመድ ገልፀዋል፡፡

ህዳር 29 ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እውቅና የሰጠ  ህገ መንግስት የፀደቀበት እለት መሆኑን የገለፁት ምክትል አፈ ጉባኤው፤ በዓሉ የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት ይበልጥ  የሚያጠናክር እና እርስ በእርስ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ አንድነታችን  በዓመት አንዴ የሚከበር  ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ልናከብረውና ልናጠናክረው  የሚገባ ነው" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባለን ማህበራዊ መስተጋብሮቻችን  እርስ በእርስ  በመቻቻል፤ በመከባበር እንዲሁም አንድነታችንን በማጠናከር ለአገራችን ብልጽግና መስራት ይገባል ሲሉም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም