ትውልድ ገዳይ አገር አፍራሽ

290
  • ሙስና ዓለማችንን ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከበሽታና ከተፈጥሮ አደጋ ባልተናነሰ እየናጣት እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።
  • በዓለማችን በዓመት ከአንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ለጉቦ ይውላል።
  • በኢትዮጵያ ሙስና የደህንነት ስጋት ሆኗል።
  • ለሉዓላዊነታችን በጋራ እንደቆምን ሁሉ ሙስና ላይ መዝመትም አሁናዊ የጋራ የትግል መስመራችን መሆን ይገባዋል።

አልበርት አንስታይን “የሰው ልጆች በምድር ላይ ለመኖር በእጅጉ የሚቸገሩበት ወቅት የሚሆነው ሰይጣናዊ ስራዎች ነግሰው እምነት ማጉደልና ሙስና ጥፍራቸውን ዘርግተው ሁሉን መቧጠጥ የጀመሩ ጊዜ ነው” ብሎ ነበር። ያጊዜ ትላንት፤ ያጊዜ ዛሬ መሆኑ በተግባር ታይቷል። ሰይጣናዊ ስራዎች አይለው የሙስና ጥፍሮችም ብዙዎችን ቧጠው አገር አውድመዋል። ጥያቄው ያ ጊዜ ነገን  እንዳይሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው የሚለው ይሆናል።

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል “the impact of corruption on growth and inequality” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ2014 ባካሄደው ጥናት እንዳሰፈረው ሙስና ማለት ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ስርዓቶችን፣ ህጎችን፣ ደንቦችን፣ አሰራሮችንና መርሆችን መጣስ ነው። ማጥፋት፣ ማበላሸትና ህግን ጥሶ አምባገነናዊ አሰራርን መከተል የሙስና የበኩር ልጆች ናቸው።

ሙስና ዓለማችንን ከጦርነት፣ ከረሃብ፣ ከበሽታና ከተፈጥሮ አደጋ ባልተናነሰ እየናጣት እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ዓለም ባንክ እ.አ.አ. በ2017 ኮምባቲንክግ ኮራፕሽን (Combating Corruption) በሚል ባወጣው ዘገባ ላይ እንዳመላከተው በዓለማችን ግለሰቦችና የንግድ ተቋማት በዓመት ከአንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ጉቦ ይከፍላሉ።  

አብዛኛው ገንዘብ የሚከፈለው በድሆች መሆኑ ነው። ለምሳሌ በሴራሊዮን ደሃው ማህበረሰብ ከገቢው 13 በመቶ የሚሆነውን ጉዳዩን ለማስፈፀም በጉቦ መልክ ለመስጠት ይገደዳል። በፓራጓይም በተመሳሳይ ደሃው የህብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ እየተመዘበረ መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

በአገራችን ያለው ሁኔታም የተለየ አለመሆኑን ከህዝብ የሚነሱ ሮሮዎችን በማጤንና በተለያዩ ጊዜያት የተወሰዱ እርምጃዎችን መለስ ብሎ በመመልከት ብቻ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። የህዝብ ሀብትና ስልጣንን ለግል ጥቅም ሲያውሉ ሀፍረት የሚባል የማይሰማቸው ህሊና ቢሶች እዚህም እዚያም ሞልተዋል። ወገኖቻቸው የዕለት ጉርስ አጥተው የሚቀምሱትን እየናፈቁ፤ በእርዳታ የተገኘን እህል ሳይቀር የሚቀራመቱ ብዙዎች ናቸው።

ለሰው ልጆች የከፋ የድህነት መንስኤ ሆነው የሚጠቀሱትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች በማባባስ በቀዳሚነት ከተፈረጁት ምድራዊ (ሰይጣናዊ) ድርጊቶች መካከል ሙስና አንደኛው መሆኑን የተለያዩ ምሁራን በጥናት አረጋግጠዋል።  

“የሁሉም የሆነ የማንም አይደለም” እንደሚሉት ሩሲያውያን በብሂላቸው፤ የሙስና ወንጀል በቀጥታ በአንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ላይኖር ወይም የአጭር ጊዜ ተጽእኖው ላይታይ  ይችላል፤ በህዝብና በአገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ግን በዋጋ ከመተመን ያለፈ ይሆናል።  

ነገር ግን ግለሰቦች በቀጥታ ተጠቂ ባለመሆናቸው አፍንጫቸው ስር የሙስና ወንጀል እየተፈፀመ እያዩም የነርሱ ጉዳት ስለማይመስላቸው ጉዳዩን ለህግ በመጠቆም አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ አያደርጉም። ይህ ደግሞ ሙስና ጥፍሩን አሹሎ በአደባባይ እንዲመጣ እድል ሰጥቶታል።  

ሙስና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ያዛባል፤ የአገር ሀብት ተጠቃሎ በተወሰኑ ግለሰቦች ኪስ እንዲገባና ያለአግባብ እንዲባክን መንገድ ይከፍታል፤ አድሏዊ አሰራርን አስፍኖና ፍትህን አዛብቶ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት በመሸርሸር ረገድም ተወዳዳሪ የለውም።

አፍሪካ ኢንስቲትዩት ኦፍ ማኔጅመንት፣ ዴቬሎፕመንት ኤንድ ገቨርናንስ የተሰኘ ተቋም በአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ያጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው በአፍሪካ የሚፈፀመው ሙስና በየዓመቱ አህጉሪቷን 148 ቢሊዮን ዶላር ያሳጣታል። እንግዲህ የአፍሪካ ህዝብ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከሚያሳርፉበት አለንጋና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቹ ከሚቀጡት ቅጣት ባልተናነሰ በሙስና የሚደርስበት ድቆሳ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ከአገራዊ ለውጡ በፊት በ20 ዓመታት ውስጥ በህገ- ወጥ መንገድ ከአገር የወጣው ገንዘብ 30 ቢሊዮን የአሜርካ ዶላር ይሆናል። ይህ ገንዘብ ለ100 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በነፍስ ወከፍ ቢከፋፈል እንኳን እያንዳንዱ ከ7 ሺ 200 ብር ያላነሰ ገንዘብ ይደርሰው ነበር ማለት ነው። ይህ የሙስና ጥፍር ዛሬም ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል።

ሙስና ምን ያህል የሀገር ደህንነት ስጋት እንደሆነ በቀላል ምሳሌ እንመልከት። ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት አንድ አጠቃላይ ሆስፒታል ለመገንባት አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል። አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ገንብቶ ለማጠናቀቅም 30 ሚሊዮን ብር ይፈልጋል። አንድ ጤና ጣቢያ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን አንድ ጤና ጣቢያ ለ25ሺ፣ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለ100 ሺ እንዲሁም አንድ ጠቅላላ ሆስፒታል ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ እንዲያገለግሉ ታስበው የሚገነቡ መሆናቸውን ነው።

ታድያ በየዓመቱ አገርና ህዝብ በሙሰኞች የሚያጡት ገንዘብ ስንት ሆስፒታል በገነባ፤ ስንት ሰዎችን ከህመማቸው በፈወሰ፤ ስንት ዜጎችን ከድንቁርና ባላቀቀ ነበር። ለዚህም ነው ሙስናን ከሰይጣናዊ ተግባር የተቆራኘ የብዙዎችን ልብ እየፋቀ የሚያደማ ጥፍራም መባሉ።   

የሙስና ወንጀል በሃገርና በህዝብ ላይ የሚፈፀም በመሆኑ “ተጐጂ ነኝ” ብሎ በባለቤትነት ብዙ ለህግ የሚያቀርብ አካል የለም። የሙስና ተግባርን ከማጋለጥና ከማውገዝ ባህላችን ጋር ያለው ነገር ደካማ መሆኑ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አይነት እንዳደረገው ብዙዎች ይናገራሉ።  

ህብረተሰቡ እንደ ግድያና አስገድዶ መድፈር ያሉ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ሲሰማ ሲዘገንኑትና ሲያወግዛቸውም ጭምር ይስተዋላል። በአንፃሩ ሙስና የፈፀመውን ሰው እንደ ብልህና ቀልጣፋ በመውሰድ ሲያበረታታ በሌላ በኩል ደግሞ ሙስናን ለማጋለጥ የተነሱ ሰዎችን በምቀኛነት በመፈረጅ ከማህበሩ ሲያገል ይታያል።

“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለዉ አባባል ከብሂልነት አልፎ በተግባር በነገሰባት አገራችን የሙስና ወንጀልን ማጋለጥ መመርመርና አጥፊዎችን ለህግ አቅርቦ ማስቀጣት አስቸጋሪ ሆኗል። ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ "የገጠመንን ሀገራዊ ችግር እንደ እድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል" በማለት የተናገሩት።

ሙስና የሀገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ መሆኑን መንግስት በሚገባ ተረድቷል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ይህንኑ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ሌብነት አታካች ሆኗል' በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይል በእግር አይሄድም የሚለው የተለመደ መሆኑን አንስተዋል። አክለውም ሌብነት ከልምምድ ባሻገር እንደመብት እየተቆጠረ መሆኑ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል ብለዋል።

የሙስና መዘዘ ብዙ ነው። ህገ-ወጥነትና ወንጀልን ያስፋፋል፤ የሀገርን መሠረተ ልማት ውጤታማነት ያቀጭጫል፤ የመንግስት አስተዳደር ታክስ እና ክፍያ የመሰብሰብ አቅም በማዳከም የታክስ ገቢን ይቀንሳል፤ ትምህርት፣ ጤና እና ሌሎች የህብረተሰብ መሰረት የሆኑ አእምሯዊና ቁሳዊ ልማቶች እንዳይስፋፉ ያደርጋል፤ ዜጎችን ተስፋ ያስቆርጣል፤ እየከፋ ሲሄድም አገር ያፈርሳል።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሙስናን መከላከል ላይ የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባ የገለጹት። ሌብነት የኢኮኖሚ እድገት ነቀርሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰው ሌብነትን ለመግታት በካቢኔ ደረጃ ከፍተኛ ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል። በዚህም ብሔራዊ የፀረ- ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ ምርምራ እያደረገ መሆኑን በማንሳት፤ በቅርብ ቀናትም ብሔራዊ ኮሚቴውን ይፋ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚጀመር ጠቁመው ነበር።

በምክር ቤቱ ፊት ላነሱት ሀሳብ ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል። የኮሚቴው አባላት ስብጥር ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አገልግሎት፣ ከስነ- ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ወዘተ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ አንዳች የተጠናከረ ስራ ለመስራት ያለውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

የፀረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴው የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት እንዲችል የኅብረተሰቡ ሙሉ ትብብር ወሳኝ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ ለብሔራዊ ኮሚቴው በመላክ ሙስናን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል፡፡   

ይህን የሚያደርገውም ለራሱና ለአገሩ ሲል መሆኑን መረዳት ያሻል። ምክንያቱም የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን እ.ኤ.አ በ2009 እንደተናገሩት “የህዝብና የመንግስት ገንዘብ በሙስና ተጠፍሮ ለግል ጥቅም ከዋለ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶች፣ እና ሌሎች ለህብረተሰቡ አስፈላጊ የሆኑ ግንባታዎች የሚከናወኑበት ገንዘብ አይኖርም ማለት ነው።”

የሙስና መስፋፋት በአንዲት አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አካባቢያዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ በርካታ አሉታዊ ገጽታዎች እንዳሉት ከተጨባጭ ማነቆዎቹ በመነሳት መገንዘብ ተችሏል። የዲሞክራሲ ዕድገትና የህግ የበላይነትን ይገድባል። ሞራሉና ግብረ-ገባዊ ብቃቱ የወረደ ህብረተሰብ እንዲፈጠርም ምክንያት ይሆናል። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ይህን አይነት ውድቀት እምቢ ማለት ይገባቸዋል።

ዝቅተኛ ሙስና (petty corruption) ከፍተኛ ሙስና (Grand corruption) እና ፖለቲካዊ ሙስና (Political corruption) የተሰኙ ሶስት የሙስና አይነቶች በሁሉም አገሮች ይብዛም ይነስም እንደሚታዩ የተለያዩ መፃህፍትና የጥናት ውጤቶች ይመሰክራሉ። አሁን አማራጩ አንድና አንድ ብቻ ነው። ከሙስና የፀዳች አገር እንድትኖረን ከፈለግን ለዚህ ሰይጣናዊ ድርጊት በር የሚከፍቱ ጉዳዮችን በሙሉ ተረባርቦ መዝጋት የግድ ይላል።  

ሙስና የሰው ልጅ በምድር ላይ የጋራ ኑሮ ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ ዛሬን የዕድገትና የልማት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር እንቅፋት በመሆን መጪው ጊዜያችንንም የስጋትና መሳቀቅ እንዳያደርግብን በጋራ ተረባርበን ልናቆመው ይገባል።

መንግሥት በየደረጃው የሚገኘውን መዋቅር በመፈተሽ፣ በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ አመራሮችንና ሌሎች ተዋንያንን ለሕግ በማቅረብ፣ ለሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በጥናት በተደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ መገለጹም የጸረ- ሙስና ትግሉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ አንድ እርምጃ ነው፡፡

መንግሥት በጸጥታው ዘርፍ እንዳደረገው ሁሉ በሙስና ላይ ጠንካራና የማያዳግም ኦፕሬሽን ማድረግ እንዳለበት የጥናቱ ውጤትና የሕዝብ ውይይቶች ግምገማ ማመላከቱ መገለጹ ደግሞ አንድ የትግል መስመር እንደሚጠብቀን ያሳያል።

ኤድዋርድ ጌቦን የተባለ የኢኮኖሚ ተንታኝ እንደሚለው መንግስታዊ ነፃነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአደጋ መጋለጡን የሚያሳብቁ ምልክቶች የሚገኙት ሙስና በተስፋፋበት ዘመን ነው። እናም ለሉዓላዊነታችን በጋራ እንደቆምን ሁሉ ትውልድ ገዳይ አገር አፍራሽ የሆነው ሙስና ላይ መዝመትም አሁናዊ የኢትዮጵያውያን ጋራ ትግል መስመራችን መሆን ይገባዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም