የኬንያ ታዋቂ አትሌቶች በታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ይታደማሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኬንያ ታዋቂ አትሌቶች በታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ይታደማሉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 9 ቀን 2015 የኬንያ ታዋቂ አትሌቶች በታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት እንደሚታደሙ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታወቀ።
በዚህም ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ የ2015 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ በክብር እንግድነት ይታደማሉ።
ውድድሩ ከነገ በስቲያ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ይካሄዳል።
ኬንያዊ አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር በውድድሩ ላይ ለመታደም ዛሬ አዲስ አበባ መግባቷን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ፔሬስ እ.አ.አ. በ2016 እና 2020 ሁለት ጊዜ የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸናፊ ሆናለች።
ሌላኛው የኬንያ የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ሞሰስ ታኑይ በውድድሩ ላይ እንደሚገኝም ነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያስታወቀው።
የ57 ዓመቱ ታኑይ በ1993 በጀርመን ስቱትጋርት በተካሄደው አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን ተከትሎ ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል።
ሞሰስ ታኑይ በኬንያ ኤልዶሬት ከተማ የሚካሄደው የማራቶን ውድድር ዋና አዘጋጅ ነው።
ከኬንያውያን አትሌቶች በተጨማሪ ሁለት የዩጋንዳ አትሌቶች በእሁዱ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ተገልጿል።
ለውድድሩ ሽፋን ለመስጠት ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣን ጨምሮ ሌሎች የኬንያ መገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባ መግባታቸውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል።