ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት የድርሻችንን እንወጣለን... በጂንካ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ስምምነቱ ገቢራዊነት የድርሻችንን እንወጣለን... በጂንካ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች

ጂንካ ህዳር 9 ቀን 2015 (ኢዜአ) በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው በጂንካ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች አስታወቁ።
የክልሉ ተወላጆች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው ስምምነት ስኬት የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስትና ህወሓት የሰላም ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ስምምነቱን ለማጽናት መንግሥት የጀመራቸውን ሥራዎች አድንቀዋል።
በጂንካ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች መካከል ቀሲስ ገብረኢየሱሰ ተስፋዬ አንዱ ናቸው።
ቀሲስ ገብረኢየሱሰ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "በሰላም ስምምነቱ ደስተኞች ነን፤ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተፈፃሚ እንዲሆኑ እንሻለን" ብለዋል።
"ሰይጣናዊ ሀሳብ ካለው በቀር ሰላምን የሚጠላ የለም" ያሉት ቀሲስ ገብረኢየሱስ፤ "የጦርነትን ሰቆቃ አሳልፎ የሰላም አየር መተንፈሳችን አስደሳች ነው" ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ከግጭትና ከጥላቻ የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ገልጸው፤ ጥላቻና መገፋፋትን በማስወገድና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ መክረው፤ እሳቸውም ለዘላቂ ሰላም እንደሚጸልዩም አረጋግጠዋል።
"በተለይም ከፍረጃና ከጥላቻ አስተሳሰብ በመውጣት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር አንድነታችንን ልናጎለብት ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።
ቀሲስ ገብረኢየሱሰ አክለውም "የሰላም ስምምነቱ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር መሰረት ይጥላል" ብለዋል።
ዜጎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና ልማት እንዲፋጠን ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም በቀና አስተሳሰብ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ድጋፍ እንዲያደርግ መክረዋል።
የትግራይ ክልል ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ እንዲነጠልና የተገኘውን የሰላም አየር እንዳይተነፍስ አሁንም እየሰሩ ያሉ አንዳንድ አካላት ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ቀሲስ ገብረኢየሱስ አሳስበዋል።
የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት አበክረው እንደምሰሩም አረጋግጠዋል ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ።
ወይዘሮ አብርሂት ተክለይ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሰላም አየር በመምጣቱ በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋ።
የሰላም ስምምነቱ ጸንቶ በችግር ውስጥ የቆዩ ዜጎች እፎይ እንዲሉ ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ካሉ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከተገናኙ ከሁለት ዓመት በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በስምምነቱ የመጣው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
መንግሥት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና ሰበዓዊ ድጋፎችን ለማዳረስ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑንም ወይዘሮ አብርሂት ተናግረዋል።
"የሰላም ስምምነቱን በጉጉት ስጠብቀው ነበር፤ የፌደራል መንግሥትና ህወሓት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ከምንም በላይ ደስተኛ ነኝ" ያለው ደግሞ ወጣት መሀሪ ገብረጊዮርጊስ ነው።
ለሀገር ሰላም፣ ሉዓላዊነትና ደህንነት ሲባል ስምምነት የተደረሰባቸውን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም ተናግሯል።
"ከሰላም የሚገኘው ትሩፋት ብዙ በመሆኑ የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ሲልም ገልጿል።
የፌደራል መንግሥትና ህወሓት ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በአፍሪካ ሕብረት አወያይነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።