ኒውክሌርን ጨምሮ አማራጭ ዕምቅ የኃይል ምንጮችን መጠቀም የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ኒውክሌርን ጨምሮ አማራጭ ዕምቅ የኃይል ምንጮችን መጠቀም የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጀ
ህዳር 9/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኒውክሌርን ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ዕምቅ የኃይል ምንጮችን መጠቀም የሚያስችል ፖሊሲ መዘጋጀቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዘርፉ ተቋማት ጋር በመሆን በተሻሻለው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ተወያይቷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በዚሁ ወቅት፤ በ1986 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ፖሊሲ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የማሻሻያ ዝግጅት ሲደረግበት መቆየቱን ገልጸዋል።
ፖሊሲውን ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ከአረንጓዴ ልማት፣ ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ለማጣጣም መከለስ አስፈልጓል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በማያደርሱ የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በማተኮር በቀጣናው የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ማጠናከርና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግ የረቂቅ ፖሊሲው ትኩረት ነው ።
ረቂቅ ፖሊሲው ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ጨምሮ ዘመናዊ እና አዳዲስ የኢነርጂ ዘርፎች ላይ ማተኮርና ከውጭ የሚገባን ኃይል በአገር ውስጥ መተካት ሌላው ግብ መሆኑን አክለዋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂኔር ሱልጣን ወሊ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሁሉም የኃይል አማራጮች ዕምቅ እቅም ቢኖራትም እስካሁን 98 በመቶው ከታዳሽ ኃይል የሚመነጭ ነው።
ከውሃ ኃይል ብቻ 45 ሺህ ጊጋ ዋት የማመንጭት አቅም ቢኖራትም፣ እስካሁን ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት ያልበለጠ ኃይል ነው ያመነጨችው ብለዋል።
ለዚህ ውስን አቅሟ አንዱ ምክንያት ደግሞ የግሉ ዘርፍ በኃይል ማምረትና አቅርቦት ላይ ባለመሳተፉ እንደሆነ ገልጸው፤ ረቂቅ ፖሊሲው ለመንግስትና ለግሉ ዘርፍ አጋርነት ምቹ ሁኔታ ማስቀመጡን አንስተዋል።
ፖሊሲው በቀጣይ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የታዳሽ ኃይል ዘርፎችን ለመጠቀም እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ ለአብነትም ኒውክሌርን ለኃይል ምንጭነት ለመጠቀም መሰረት የሚጥል እንደሆነ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ታዳሽ ኃይል እና ውሃን በመጠቀም የሚመነጨውን ግሪን ሃይድሮጅን የተሰኘውን የኃይል አማራጭ በመጠቀም በግብርናው ዘርፍ በተለይም ለአፈር ማዳበሪያ ዝግጅት ማዋል በፖሊሰው ተቀምጧል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥራትና አስተማማኝነት፣ የኃይል ብክነት ቅነሳ፣ በዘርፉ ጤናማ ፋይናንስ መፍጠር፣ ባህላዊ ባዮማስ አጠቃቀምን ማስተካከል፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ቁጥጥር ማጎልበት፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅምን ማጎልበት ረቂቅ ፖሊሲው ካካተታቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ተጠቅሰዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው በሁለት ወራት ውስጥ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል።