ቀጥታ፡

መንግስት በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት የሲቪል ማህበራት ማገዝ አለባቸው - ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 8/2015 መንግስት በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት የሲቪል ማህበራት በግንባር ቀደምትነት ማገዝ እንደሚኖርባቸው የፍትህ ሚኒስትር እና የፌደራል መንግስት የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባል ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ገለጹ፡፡

የሲቪል ማህበራቱ በበኩላቸው የፌደራል መንግስትና ህወሃት የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አድንቀው፣ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የፍትህ ሚኒስትር እና የፌደራል መንግስት የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባል ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ጥቅት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተፈረመው የሰላም ስምምነት ሂደት፣ ውጤት እና አንድምታ ዙሪያ ለሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ባስከበረ መልኩ መጠናቀቁን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በዚህም ኢትዮጵያ እና መላው ኢትዮጵያውያን ማሸነፋቸውን በማንሳት።

የሰላም ስምምነቱ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና በግዛት አንድነት ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ በመቀልበስ ግጭቱን በዘላቂነት በማቆም ዜጎች እፎይታ እንዲያገኙ የማድረግ ግብ እንደነበር ገልጸዋል።

በግጭቱ በዜጎች ላይ የደረሰውን የህይወት፣ የአካል፣ የስነልቦና፣ እንዲሁም ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአካባቢውን ማህበረሰብ መልሶ ለማቋቋም ምቹ ሁኔታ መፍጠርም የሰላም ንግግሩ ዋና ዓላማ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ከግጭቱ ጋር በተገናኘ በአገር ኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲ ላይ ተደቅኖ የነበረውን ፈተና ማስወገድ የኢትዮጵያ ፅኑ አቋም ነው ያሉት ዶክተር ጌዴዮን፤ በሰላም ስምምነቱም ግቦች መሳካታቸውን አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ እስካሁን በቆመችለት የሰላም ጥሪና በመርሆዎቿ ሙሉ መፅናቷንና የሰላም አማራጩ መሳካቱን ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የአገልግሎት ማስጀመር፣ የመልሶ ግንባታና መሰል ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል ማህበራት በሀገር ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት በግንባር ቀደምትነት ማገዝ እንዳለባቸውም ነው ዶክተር ጌዲዮን ጥሪ ያቀረቡት።

በተለይም በዜጎች ላይ የደረሰውን የስነ-ልቦና ጉዳት ለማከም እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ሂደቱ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በመጠቆም።

ለዚህም ሃብት በማሰባሰብ የትምህርት ተቋማትን፣ የጤና ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሀገራዊ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው፤ የሰላም ስምምነቱ ተተግብሮ ህዝቡ በዘላቂነት እፎይታ እንዲያገኝ የሲቪል ማህበራት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

ለዚህም መንግስት የሚያደርገውን የመልሶ ግንባታ ስራን መደገፍን ጨምሮ በሁሉም መስክ በትኩረት እንዲሰሩ ነው የጠቆሙት፡፡

በማብራሪያው ላይ የተገኙ ሲቪል ማህበራት አመራሮችና ተወካዮች በሰጡት አስተያየት የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በተግባር ማሸነፏን ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም ወገን ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ የሲቪል ማህበራት የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የሰላም ስምምቱ በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት መሆኑንን በማውሳት።

መንግስትና ህወሃት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም