አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በ2016 ዓ.ም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በ2016 ዓ.ም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊሆን ነው

ሐዋሳ ህዳር 8/2015 (ኢዜአ) አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በ2016 ዓ.ም ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በተያዘው ዓመት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መስጠት እንደሚጀመር ገልጿል።
31ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዩኒቨርሲቲዎች ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍና በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ማስቻል እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል እንደሚገኙበት አመልክተዋል።
''በሁለት ወር ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ሆኖ ይደራጃል'' ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት እንዲሁም በአራት ዓመት ውስጥ ሁሉም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ እቅድ ተይዟል ብለዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የመውጫ ፈተና መስጠት ከተያዘው ዓመት ጀምሮ መስጠት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አዲስ ስርዓተ ትምህርት መቀረጹን አስታውሰዋል።

ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በሙከራ ደረጃ የተጀመረው አዲሱ ስርዓት ትምህርት ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ስርዓተ ትምህርቱ ዘንድሮ በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ በ2016 ዓ.ም ወደ ሙሉ ትግበራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
31ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በ2014 ዓ.ም በትምህርቱ ዘርፉ በተደረጉ የለውጥ ስራዎችና አፈጻጸም እንዲሁም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
እስከ ሕዳር 10 ቀን 2015 በሚቆየው ጉባኤ ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሆኑ ከ400 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተነግሯል።