የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተግባርን በፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ተግባርን በፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 8/2015 የውጭ ግንኙነት የሀገር አቅም ነፀብራቅ በመሆኑ የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲን አስተባብሮ በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ ተገለፀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለዲፕሎማቶቹ በዲጂታል ዲፕሎማሲ እና አዲሱ ሚዲያ ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ማከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያለመ መሆኑ ተነግሯል።
በዲጂታል ዲፕሎማሲ እና አዲሱ ሚዲያ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ ዲፕሎማቶች ሚዲያውን ለዲፕሎማሲ መጠቀም አለባቸው ብለዋል።
መሠረታዊ የሚዲያ ዲፕሎማሲ እውቀት እና የአዲሱ ሚዲያ አጠቃቀም ክህሎትን ማዳበር እንደሚገባቸው በመጠቆም።
አዲሱ ሚዲያ በማህበራዊ ትስስር ገጾች መረጃዎችን በቀላሉ ለበርካቶች ተደራሽ ለማድረግ ምቹ በመሆኑ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚዲያ ዲፕሎማሲ ለማስከበር ትልቅ አቅም ይሆናል ነው ያሉት።
የውጭ ግንኙነት የሀገር ውስጥ አቅም ነፀብራቅ በመሆኑ የፐብሊክ እና የዲጂታል ዲፕሎማሲ በማስተባበር የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር እንደሚገባ አብራርተዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ኩራባቸው ትርፌሳ እና ሙሉጌታ ተሾመ፤ ከዘመኑ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ቀልጣፋና ውጤታማ ዲፕሎማሲ ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል።
በስልጠናው በዲጂታል ዲፕሎማሲ እና አዲሱ ሚዲያ ላይ በቂ ግንዛቤና እውቀት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰሩ አንስተዋል።
በተለይም ከአጀንዳ ተቀባይነት ወጥቶ የራስን አጀንዳ ወደመስጠት በመቀየር የውጭ ግንኙነት ስራዎችን ስኬታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።