የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል -ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል -ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ ህዳር 8/2015/ኢዜአ/ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ባለፈ ዜጎችን በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ኮሚሽኑ የተረጅነት አስተሳሰብን መቀየር፣ የአደጋ ቅደመ መከላከልና ምላሽ አሰጣጡን ማጠናከር እና የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የፖሊሲ ማሻሻያ እያደረኩኝ ነው ብሏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽንን የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች በቂ ድጋፍ እንዲቀርብና ሰብዓዊ ድጋፎች ለተጎጂዎች በአግባቡ እንዲሰራጩ ከማድረግ አንጻር ስለተሰሩ ተግባራት ኮሚሽኑን ማብራሪያ ጠይቀዋል።
የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም በአማራ፣የትግራይና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአማራና አፋር ክልሎች በ17 ከባድ ተሽከርካሪዎች የጥራጥሬና የአልሚ ምግቦች ድጋፍ ለተጎጂዎች መድረሱን ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
በትግራይ ክልልም ድጋፉን የሚያስተባበሩ ሶስቱ ቡድኖች ተዋቅረው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ወደ ክልሉ በ80 ተሽከርካሪዎች የተጫነ ድጋፍ እንዲቀርብ መደረጉን ተናግረዋል።
በፌደራል መንግስትና በሕወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎም ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የሕክምና ቁሳቁሶችን እንዲያቀርብ አድርጓል ነው ያሉት አምባሳደር ሽፈራው።
በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወር ለ1 ነጥብ 5 ለሚሆኑ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ መደረጉንና በዚህም አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች 569 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ እንደሚያስፈልግ አመልክተው በእስካሁኑ ሂደትም 149 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ ግዢ መደረጉን ተናግረዋል።
ቀሪውን ግዢ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየሰራበት ያለውን ፖሊሲ ለመቀየር የክልሳ ስራው መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ፖሊሲው የተረጅነት አስተሳሰብን መቀየር፣ የአደጋ ቅደመ መከላከልና ምላሽ አሰጣጡን ማጠናከር እና የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ ስትራቴጂክና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አይድሩስ ሀሰን፤ ኮሚሽኑ የሚያሰራጫቸው ሰብአዊ ድጋፎች በአግባቡ ወደ ሚፈለገው ቦታ መድረሳቸውን የሚያረጋግጥበት የክትትል ስርዓት ዘርግቷል ብለዋል።
በየወቅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ውስጥ የገቡ ዜጎችን ለመደገፍና የበለጠ የምግብ ክምችት እንዲኖር ለማድረግ ተጨማሪ መጋዘኖች የመገንባት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ ኮሚሽኑ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ የሰው ኃይል እና የቁሳቁስ የማደራጀት ተግባር ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል።
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት እየተገበራቸው ያሉ የማሻሻያ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ያሉት ዶክተር ዲማ ቋሚ ኮሚቴው የተቋሙን ተግባራት በቅርበት እንደሚደግፍ ተናግረዋል።