ቀጥታ፡

የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ለአገራዊ ፖሊሲዎች ዋነኛ ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ /ኢዜአ/  ህዳር 8/2015 የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ለአገራዊ ፖሊሲዎች ዋነኛ ግብዓት ማዋል እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ቀን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡

በዚሁ ወቅት እንደተገለጸውም ጥራት ያለው ስታቲስቲክስ መረጃዎች ለፖሊስ ማውጣት፣ ለአገራዊ ዕቅድ፣ ለፕሮጀክት ዝግጅትና ለልማት ስራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነመራ ገበየሁ አገራዊ የስታቲስቲክስ  አቅምን ለመገንባት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።  

በዚህም ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ማደራጀት፣ ተቋሙን ሪፎርም ማድረግን ጨምሮ የተቋሙን ስያሜ የመቀየር ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡

እያደገ የመጣውን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት መረጃን የማመንጨት፣ የማደራጀት እና  በቴክኖሎጂ የማዘመን ተግባራትም እየተናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመንግስት አስተዳደራዊ ተቋማት ያሉ መረጃዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ገልጸው፣ ይህን ለመቅረፍም አገልግሎቱ ራሱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በቴክኖሎጂ የተደራጀ የስታቲስቲክስ መረጃ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም፡፡ 

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ላለፉት 60 ዓመታት ለመንግስት እና ለሌሎች አካላት መረጃዎችን በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ጥራት ያለውን መረጃ በተቀናጀና ወጥነት ባለው መልኩ ለመንግስት በማቅረብ ውጤታማ አገራዊ ፖሊሲዎች እንዲዘጋጁም ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም