ቀጥታ፡

ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በ121 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እየተካሄደ ነው- ማእከሉ

ወልዲያ (ኢዜአ) ህዳር 8/2015  የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በ121 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የምርጥ ዘር ብዜት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

የምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አካሉ ገብሩ ለኢዜአ እንዳሉት የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ የሰብል ዝርያዎች እየለሙ ነው።

በተለይም ለአካባቢው የአየር ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ ማሽላ፣ ስንዴና ጤፍ ምርጥ ዝርያዎችን በ121 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የማባዛት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በራያ ቆቦ፣ በቆቦ ከተማና በዋድላ ወረዳ እየተካሄደ ባለው የዘር ብዜት ስራ 280 አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቁመው ከሚባዛው ዘር ከ3ሺህ 396 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

የማሽላ ዘሩ 50 ኩንታል፣ የጤፍ ዘሩ 18 ኩንታል፣ እንዲሁም የስንዴ ዘሩ 40 ኩንታል ምርት በሄክታር ማስገኘት የሚያስችሉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የምርምር ማእከሉ ስልጠና በመስጠት፤ የመነሻ ዘር በማቅረብ፤ የተባይ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ ለአርሶ አደሮች እገዛ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲም ከ70 ኩንታል በላይ የዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት ከማድረጉም በላይ ለአርሶ አደሮች ምክረ-ሃሳብ በመስጠት ስራውን መደገፉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ቦጋለ ሰጤ በበኩላቸው በምርምር ማእከሉና ወልዲያ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የምርጥ ዘር ብዜት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

"ምርጥ ዘር ብዜቱ ውጤታማ እንዲሆን  በምርምር ማዕከሉ፣ እንዲሁም በወልዲያ ዩኒቨርስቲና በየደረጃው በሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ተገቢው የቁጥጥርና ክትትል ስራ እየተሠራ ነው "ብለዋል።

እየተመረተ ያለውን ምርጥ ዘር ሌሎች አርሶ አደሮች በግዥ የሚያገኙበት መንገድ ከማህበራት ጋር በቅንጅት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ እየተባዛ ካለው ከስንዴ ምርጥ ዘር 40 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ የገለጹት ደግሞ በዋድላ ወረዳ 019 ጥምጥማት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እታለሙ ወርቁ ናቸው።

ከዚህ በፊት ከሚዘሩት ዝርያ ያገኙት ከነበረው ምርት በእጥፍ ጭማሬ እንደሚኖረው አመላክተዋል ።

የስሪንቃ ምርምር ማዕከል፣ የወልዲያ ዩኒቨርስቲ፣ እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች እያደረጉላቸው ባለው ድጋፍ ውጤታማ እንደሚሆኑ ተስፋቸውን ገልጸዋል ።

በምርጥ ዘር ልማት ተሳታፊ መሆናቸው ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሚሆናቸው ያላቸውን ተስፋ የገለፁት ደግሞ በራያ ቆቦ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላ መንገሻ ናቸው።

በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ እያባዙ ካለው የማሽላ ምርጥ ዘር ከ45 እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም ከሚያለሙት የማሽላ ዝርያ ከ20 እስከ 25 ኩንታል ብልጫ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የማሽላው ምርጥ ዘር ለአካባቢው አየር ፀባይ ተስማሚ መሆኑን የገለፁት አቶ ሞላ ለሌሎች አርሶ አደሮችም በመሸጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም