የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በሩብ ዓመቱ የመንገድ ፈንድ ገቢዎች 400 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በሩብ ዓመቱ የመንገድ ፈንድ ገቢዎች 400 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 8/2015 የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በሩብ ዓመቱ ከመንገድ ፈንድ ገቢዎች 400 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡
በአስተዳደሩ የመንገድ ፈንድ ዳይሬክተር ኢንጂነር ካሳሁን በጂጋ ለኢዜአ እንደጠቀሱት በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ የመንገድ ፈንድ ገቢዎች ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም 400 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
ገቢው የተጎዱ መንገዶችን በመጠገን ህብረተሰቡ ከመንገድ ዘርፍ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል።
ገቢው የሚሰበሰበው ነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ፣ ከዓመታዊ ተሸከርካሪዎች ፍቃድ ማደስ፣ ከዘይትና ቅባት ላይ ከተጣለ ታሪፍ፣ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ተሸከርካሪዎች መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አስተዳደሩ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ለሚጠግናቸው መንገዶችና ፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ህብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ በማድረግ ረጅም አገልግሎት እንዲሰጡ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡