ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የሚበዘብዙ አደገኛ ሌቦችን በጥናት ላይ ተመስርቶ እርምጃ ለመውሰድ ምርምራ ተጀምሯል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 8/2015 ኢትዮጵያን እየበዘበዙ ያሉ አደገኛ ሌቦችን በጥናት በመለየት እርምጃ ለመውሰድ ምርምራ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ለዚህም ሰባት አባላትን ያካተተ ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ህብረተሰቡ ሌቦችን በማጋለጥና ማስረጃ በማቅረብ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

ሙስና የሀገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ነው።

በኢትዮጵያም ስልጣናቸውን ለህገወጥ ዓላማ የሚያውሉ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሃብቶች የመንግስትና የህዝብ ሀብት ላይ ከፍተኛ ሌብነት እየፈጸሙ መሆኑ  በተደጋጋሚ ይነሳል።

ሙስና ሀገርን ሊያፈርስ የሚችል የደኅንነት ሥጋት መሆኑን ያስመሰከሩ ሀገሮችን በዘመናችን አይተናል፡፡

በዓለማችን የተጀመሩ ጦርነቶች እንዳይጠናቀቁ፤ ግጭቶች እንዳይበርዱ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሙሰኞች ከዚህ አይነት ቀውሶች ስለሚያተርፉ ነው፡፡

ሙስና ዛሬ ላይ ለኢትዮጵያም የደህንነት ስጋት መሆኑን መንግስት ገልጿል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ህዝቡ የመንግስት አገልግሎትን እንዳያገኝ በሌቦች እንግልት እየደረሰበት መሆኑን የምክር ቤት አባላት አንስተዋል።

በመሆኑም በየተቋማቱ የተንሰራፋውን ሌብነትን ለመከላከል መንግስት ምን የተለየ አቅድ እውጥቶ እየሰራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው 'ሌብነት አታካች ሆኗል'  ነው ያሉት።

በተለይ የገጠመንን ሀገራዊ ችግር እንደ እድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውታል ሲሉም ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይል በእግር አይሄድም በእጁ ብቻ እንጂ የሚለው የተለመደ መሆኑን በማንሳት ሌብነት ከልምምድ ባሻገር እንደመብት እየተቆጠረ መሆኑ አደገኛ ነው ብለዋል።

ሌብነት የኢኮኖሚ  እድገት ነቀርሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሌብነትን ለመግታት በካቢኔ ደረጃ ከፍተኛ ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ ምርምራ እያደረገ መሆኑን በማንሳት፤ በቅርብ ቀናትም ብሔራዊ ኮሚቴውን ይፋ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰደ እንደሚጀመር ጠቁመው ነበር።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሌብነትን ለመቀነስና ሌቦችን ለማጋለጥ ራሱን የቻለ የአገልግሎት ቢሮ ተቋቁሞ እየሰራ በመሆኑ መረጃና ሰነድ በማቀበል ሌቦችን ለማጋለጥ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለትም ሰባት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገዋል።

የብሔራዊ ከሚቴው አባላትም፡-

1. አቶ ተመስገን ጥሩነህ

2. ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ

3. አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ

4. አቶ ሰሎሞን ሶቃ

5. አቶ ደበሌ ቃበታ

6. ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ

7. አቶ አብዱሃሚድ መሃመድ ናቸው፡፡

የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት እንዲችል የኅብረተሰቡ ሙሉ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ፣ ከቂምና ከበቀል ነጻ በሆነ መንገድ፣ ለብሔራዊ ኮሚቴው በመጠቆም በጸረ ሙስና ትግሉ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ብሔራዊ ኮሚቴው የሚወስዳቸው እርምጃዎች እና የእንቅስቃሴውን ውጤት በየጊዜው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም