ኢትዮጵያና ኩዌት የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

157

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 8/ 2015 የኢትዮጵያና የኩዌት የኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጠናከር የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ መስማማታቸው ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ አል ኪውቴይቢን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ውይይቱ ሁለቱ አገራት የኢንቨስትመንት ስራዎችን በሽርክና ማካሄድ በሚቻልባቸው አማራጮች፣ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድሎች ማስተዋወቅና የአገራቱን የኢኮኖሚ ትስስር በሚጠናክርባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የኩዌት አምባሳደር ናይፍ አል ኪውቴይቢ የአገሪቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በማስተዋወቅና በማስተሳሰር የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናክር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ኩዌት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1967 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አገራቱ እ.አ.አ 1996 የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ስምምነቱ ከእ.አ.አ 1998 ጀምሮ ተፈጻሚ በመሆን ላይ ይገኛል።

ስምምነቱ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅና ጥበቃ ላይ በዋናነት ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም