ቀጥታ፡

'ደመራ'ን በመደመር ...

አየለ ያረጋል-ኢዜአ:-  የወራት ቁንጮው መስከረም ደማቅ መልኮች አንዱ ደመራ፤ በዓለ መስቀል ነው። የዕንቁጣጣሽ ተከታይ ብሔራዊ በዓል ነው-መስቀል። መስቀልና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ትስስራቸው ጥብቅ ነው። መስቀል ከመንፈሳዊ አንድምታው ባሻገር ባህላዊ ትውፊቱ በቀላሉ አይገለጽም። እንደ ኃይማኖተ አበው ሀተታ መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን፣ ለፍጡር የሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር የገለጸበት ዓርማ ነው። በዚህም መስቀልን አማኝ ምዕመናንና ካህናት የድህነትና የእምነት ምልክታቸው፤ የርኩስ መንፈስ ማባረሪያ መሳሪያቸው አድረገው ብቻ አይደለም የሚመለከቱት። ነገረ መስቀሉ እምነቱ፣ ባህሉ፣ ትውፊቱ ብዙ ነው። ኢትዮጵያዊያን በመስቀል ወራሪዎችን ድል የነሱበት፣ የጠላት ሴራ ያከሸፉበት፣ ጨለማን በብርሃን የለወጡበት የታሪካቸውና ባሕላቸው የተጋድሎ ምልክታቸው ጋር ያያይዙታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መስከረም 10 ቀን 'ተቀጸል ጽጌ' በሚል የክርስቶት መስቀል ግማድ (ቀኝ እጁ ያረፈበት ክፋይ) ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ኢትዮጵያ የገባበትን ቀን ታከብረዋለች፤ መስከረም 17 ቀን ደግሞ መስቀሉ የተገኘበትን። መስከረም 17 ቀን የሚከበረው በዓለ መስቀል ከኃይማኖቱ ይልቅ ባህላዊ ትውፊቱ ይጎላልና በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይናፈቃል። የመስቀል ክብረ በዓል መለያው ደመራው ነው። የደመራ አደማመርና ማብራት ስነ ስርዓት በሁሉም የኢትዮጰያ አካባቢዎች ተመሳሳይ እንደሆነ ደራሲ ካህሳይ ገብረ እግዚአብሄር ይተርካሉ። በትግራይ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በዋግኸምራ፣ በአዊና በከፊል ጎጃም ደመራ ማታ ላይ ተደምሮ ንጋት ላይ ይለኮሳል። በከፊል ጎጃም፣ በሸዋ፣ በአዲስ አበባ፣ በጉራጌ፣ በጋሞ፣ በወላይታና ሌሎች የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ደግሞ እንደየ አካባቢው ተለምዶ መስከረም 16 ከዕኩለ ቀን ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ ደመራው ይለኮሳል። መስቀል እንደየአካባቢውና ባህሉ የሚናፈቅበት ዕልፍ ገጽታዎች አሉት። ለምሳሌ በእኔ ገጠራማ ትውልድ ቀዬ በወፍ በረር ስገልጸው፤ በቅድመ ደመራ ሰሞን ተራራ ለተራራ፣ ወንዝ ለወንዝ፣ ቋጥኝ ለቋጥኝ በልጅነት ወኔና ስስት እንኳትናለን፤ የደመራ ግንድ፣ አደይ አበባ፣ የደቦት ደረቅ እንጨት ለመልቀም። መስከረም 16 አመሻሽ ከብቶች በጊዜ ከተሰበሰቡ፣ ወደ ግርግም ከገቡ፣ የመስከረም 16 መዓልት ለፅልመት ሲረታ የመንደሩ ወጣቶች ወደ ተለመደችዋ 'አፋፍ' እንሰባሰባለን-አፋፏ ለደመራ ትመረጣለችና። ከአጎራባች መንደሮች የተሻለ ደመራ ለመደመር እንጥራለን። እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት በጨለማ ደመራችንን ደምረን፣ የደመርነውን ደመራ እንቧለሌ ዞረን፣ ባርከንና መርቀን፣ ጨፍረን ወደዬ ቤታችን እንበታተናለን፤ ከሰዓታት በኋላ ለመገናኘት ደግሞ እንነፋፈቃለን። የመስከረም 16 አዳር እንቅልፍ ይነሳል። በሌሊት ተነስቶ፣ ችቦ አብርቶ፣ 'አዮሃ ደመራ' እያሉ ወደ ደመራው ስፍራ ለመሄድ፣ ደርሶም ደመራውን ከሌሎች አጎራባች የመንደር ደመራዎች ቀድሞ ለመለኮስ ጉጉቱ የትየሌሌ ነው። አጠባብ ላይ ከቤት ያለ ጉብል ሁሉ (ልጃገረዶችና ወንዶች) ወደ ደመራ መሄድ ግድ ይላል። ከምድጃ አልያም ከክብሪት እሳት ጭሮ ደቦቱን (ችቦውን) ይለኩሳል። ደቦቱ በእሳት ከተያያዘ በኋላ ወላጆቹን፣ ከብቶቹን፣ የጓሮ አትክልቱን፣ በደጃፍ ያሉ ሕይወታዊያንን በሙሉ "እንጎረጎባህ፤ እንጎረጎባችሁ" ይላል። ተጠያቂውም "ዓመት ዓመቱን ያድርስህ" ማለት ይጠበቅበታል። ለብሽሽቅ ከሆነ ደገሞ "ወስፋት ይላጥህ'" ማለቱ አይቀርም ይሄኔ በተቀጣጣለ ችቦ አጸፋውን የመስጠት ልምድ አለ። ከቤት ተነስተን ደመራው ከተደመረበት አፋፍ እስከምንደርስ በአንድ እጃችን መጠባበቂያ ደቦት፣ በሌላው ያቀጣጠልነውን ችቦ ይዘን የደመራ ግጥሞችን እየደረደርን እንቀጥላለን። የመስከረም እኩሌታ ውብ ማሳ ከየቤቱ ከሚወጡ የችቦ እሳት ነበልባል ብርሃን ይታጀባል። ከሚዘወተሩ ስንኞች መካከልም፡- እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ... እዮሃ አረሬ አረሬ መስቀል ጠባ ዛሬ በሸዋ በትግሬ... ይጠቀሳሉ። ከደመራው ስፍራ ስንደርስ የ'እንጎረጎባህ! እንጎረጎባሽ! እንጎረጎባችሁ' ድምጾች ይበረታሉ። ሁሉም ልጆች እስኪሰባሰቡ መልካምም ሆነ እኩይ የአጸፋ መልሶች እየተመለሱ ጥቂት ይቆያል። ደመራውን ሶስት ጊዜ 'እዮሃ አበባዬ፣ መሰከረም ጠባዬ" እና ሌሎች የራስን ደመራ የሚያሞኳሹ፣ የሌሎቹን የሚነቅፉ፣ ዘመኑ የጥጋብ ዘመን እንዲሆንና እንዲባረክ የሚመኙ ስንኞች እየተገጠሙ እንቧለሌ እንዞረዋለን። በስፍራው በዕደሜ ታላቅ የሆነ ሰው ለችቦ ማስገቢያ ክፍት በተተወው የደመራው ገጽ በኩል የተለኮሰ ደቦቱን ያስገባል። ሌላው ሁሉ እሱን ተከትሉ ወደ ደመራው ደቦቱን ይጨምራል። ደመራው መቀጣጠል ይጀምራል፣ ጭሱም ይጨሳል፣ የእሳቱ ነበልባል ከመስከረም የንጋት ውርጭና ብርድ ይገላግላል። ደመራውን ዙሪያውን ተኮልኩለን ወሬ፣ ሀሜት፣ መበሻሸቅ፣ ባለፉት ክረምት ወራት ስለነበሩ የተሳታፊዎች ገጠመኞች በአያሌው እንሰልቃለን። የተጣላም ሳይቀር ታርቆ ያወራል፣ በዛ መበሻሸቅም የሚጣላ ቡጢ የሚሰናዘርም አይጠፋም። በዚህ መልክ የደመራው አምድ (ምሰሶ) እስክትወድቅ፣ ሌሊቱ የአህያ ሆድ እስኪመስል እናነጋለን። ምሰሶው ወደዬት እንደሚወደቅ ለማየት እንጓጓለን።ወደ ምሥራቅ ከወደቀ የጥጋብ ዓመት፤ ወደ ምዕራብ ከሆነ ግን የችጋር ዓመት ተደርጎ ይገመታል። ምሰሶው ከወደቀ በኋላ ሌላ ትዕይንት ይከተላል። እንጨት ካለቀ በአካባቢው ከሚገኝ የግለሰብም ሆነ የወል ንብረት እንጨት በመስረቅ ከደመራው ላይ ይጨመራል። በቀያችን የመስቀል አንዱ ባህሉ የበቆሎ እሸት ናፍቆት ነው። በቆሎ ቢያሸትም ባያሽትም፣ ከማሳው ተዘንጥፎ ቢቀመስም ባይቀመስም በይፋ በሰፈሩ የሚቀመሰው የመስቀል ነው። እናም በሌሊት ተቧድነን በሚያመች ቦታና ማሳ በመግባት በቆሎ የመስረቅ መርሃ ግብር አለ። ባለበቆሎውም ቀን ላይ ቢሰማም እንኳን ብዙም ስለማይቆጣ ካለፍርሃት በቆሎ እሸት በበቂ ሁኔታ እንቃርማለን። በደመራው ፍም ጠብሰን እሸቱን እንበላለን። ከደመራው ዓመድ በግንባራችን ላይ የመስቀል ምልክት እናደርጋለን። የዛሬ ዓመት አድርሰኝ ስለት እንሳላለን። አሁን ሰማዩ የአህያ ሆድ መስሏል። ቀጣዩ ተግባራችን በደቦ ወደ መንደር መዞር ነው። ቀሪ ችቧችንን አቀጣጥለን እንደ ዕድር በአንድ ደመራ አባል በሆኑ ቤቶች ሁሉ እየዞርን 'እንጎረጎባችሁ' እንላለን። እንደ ከተማ ልጅ ሳንቲም አይደለም የሚሰጠው። ለዛ ብለን ባዘጋጀናት ሳህን፣ ጣሳ ወይም ሌላ መያዣ ዱቄት እንለምናለን። የበሬና የላም ስም እየጠራን፤ እንገጥማለን። ሁሉን ቤተሰብ ካዳረስን በኋላ የሰበሰብነውን ዱቄት 'ዓመት ዓመቱን ያድርሳችሁ' ከሚል ምርቃት ጋር ተሸክመን ወደ ደመራው ስፍራ እንመለሳለን። ከዛው የደመራው ጉባኤ ወስኖ ለተመረጠች ሴት ዱቄቱ ይሰጣል። አነባበሮ እንድትጋግር በወጣቶች ዘንድ ቀጭን እመቤት (ባለሙያነቷ የተመሰከረላት) ይሰጣል። የማገዶ እንጨትም ተለቅሞ ይሰጣታል። ተመራጯ ሴት ባለትዳርም ብትሆንም ባትሆንም ዳቦ ጋግራ ለአመሻሽ ለማድረስ አደራዋን ትረከባለች። የመስቀል ዕለት በጎች ታርደው፣ አረቄ ቀርቦ፣ ሰፈርተኛው ተሰባስቦ ሲጫውት ይውላል። መስቀል የወል ክብረ በዓል ነው፤ የጋርዮሽ አከባብር። በተለይም ከሰዓት ለአንዳንድ ስራ ራቅ ካለ ቦታ የሄደ ሁሉ ይሰባሰባል። አመሻሽ ላይም እንደደመራው ምሽት ዕለት ሰው ይሰባሰባል። በዚህ ዕለት የተጣላ ጎረቤት ይታረቃል፤ ያለፈው የክረምት ጨለማ ጊዜያት ክፉ ደግ ጉዳዮች ይወራሉ። ልጆች ይቦርቃሉ። የጠዋት አደራ ተቀባይ ሴት የጋገረችውን አነባብሮ (መክፈልትም እንለዋለን) ታመጣለች። እነዚህ ከመስቀል ጥቂት የኔ ቀዬ ገጽታዎች መካከል ናቸው። እናም መስቀል ከእንቁጣጣሽ በበለጠ መልኩ በኛ መንደር ይናፈቃል.... መስቀል በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ርዕሰ ዓውደ ዓመት ይመስላል። በደቡብ ኢትዮጵያ መስቀል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባህላዊ ጎኑ ይጎላል። ጉራጌዎችና ጋሞዎች መስቀልን ከሁሉም በዓላት የበለጠ ይናፍቁታል። የተራራቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት የፍቅር፣ የደስታና የእርቅ በዓል ነው-መስቀል። በጋሞ ብሔረሰብ ባሕል በዋዜማው ሰው ቢሞት አንኳን በሌሊት ተወስዶ ይቀበራል እንጂ ለቅሶ እንደማይለቀስ ይነገራል፤ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱም ልዩ መኖ እንደሚቀርብላቸው ይነገራል። ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው በጋሞዎች ደግሞ 'ለመስቀል ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ' በሚመሰል መልኩ የባሀል ልብስ አለባበስ እንደሚዘወተር መምህር ካህሳይ (በህብረ ብዕር ድርሰታቸው) ጽፈዋል። መስቀል በጉራጌዎች ዘንድ አውራው በዓል ነው። ለቀጣዩ መስቀል ዝግጅት የሚጀመረው የአሁኑ ባለፈ ማግስት ነው። ሁሉም የየራሱን ዝግጅት ያደርጋል አባወራ ሰንጋ ለመግዛት፣ እማወራ ማጣፈጫውን ለማዘጋጀት፣ ወጣቶች ደመራና ደቦት ለማዘጋጀት፣ ልጆች ምርቃት ለመቀበል የየራሳቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። መስቀል ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የሚጠያየቅበት፣ ለትዳር የደረሱ ሚስት የሚያጩበትና የሚመርጡበት ጥላቻና ቂም በፍቅርና በይቅርታ የሚታደስበት ነው። ይህም በመሆኑ በጉራጌዎች ዘንድ መስቀል ትልቅ ቦታ የሚቸረው ዓውራ ብሔራዊ በዓል ነው። ደመራ በከተሞች ደማቅ ነው። በዓለ መስቀል ግን በአብዛኛው የጋርዮሽ ሳይሆን የተናጠል አከባብር ይስተዋልበታል። በዓለም የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት የተመዘገበው መስቀል በአዲስ አበባ የደመራ በዓል በብሔራዊ ደረጃ በ'መስቀል አደባባይ' ይከበራል። የመንግስትና ኃይማኖት ተቋማት መሪዎች ይታደማሉ። የውጭ አገር ጎብኝዎች ታድመው ይደመሙበታል። ከዛሬ የደመራ ዕለት ጀምሮ የሚከበረው የዘንድሮ በዓለ መስቀል ዘንድሮ ልዩ ገጽታ አለው። ደመራ 'ደመረ፣ ተሰባሰበ' ከሚለው ስርዎ ቃል መጣ እንዲሉ ሊቃውንት በኃይማኖት አባቶች ልዩነት ለዓመታት ሲኖዶሷ ለሁለት ተከፍሎባት የነበረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የዘንድሮ ደመራን በዓል 'ምዕመኗ በውጭ አገር ለዓመታት ከቆዩ አባቶች' ጋር ተደምረው ያከብራሉ። ከ20 ዓመታት በላይ የተነፋፈቁ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦችም የጋራ ችቦ የሚለኩሱበት ዕለትም ይሆናል-የዘንድሮ ደመራ። በፖለቲካው መስክም ኢትዮጵያ ለዓመታት በአምባጓሮነት የቆዩ የውስጥም የውጭም ድርጅቶችና ግለሰቦች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ በተደመሩበት ዓመት መከበሩም ሌላው ታሪካዊ መልኩ ነው። ደመራና መስቀል የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋና፣ የተስፋ ... እሴቶች የሚገለጹበት ባህላዊና ኃይማኖታዊ ከብረ በዓል ነው። በአገሪቱ መዲና አዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ሰሞነኛ የፖለቲካና የብጥብጥ ግጭቶች የሚረግቡበት፣ ቂምና ጥላቻ የሚወገድበት፣ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ ያደረጉበት አገራዊ ለውጥ የሚቀጥልበት፣ በጎ በጎ የሚሰማበት የአንድነት ዓመት እንዲሆን ምኞታችን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም