ለሶስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ፖሊሲ ሊሻሻል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሶስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ፖሊሲ ሊሻሻል ነው
አዲስ አበባ/ኢዜአ/ ህዳር 8/2015 የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሶስት አስርት ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኢነርጂ ፖሊሲ ሊሻሻል መሆኑን አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ከዘርፉ ተቋማት ጋር በመሆን በተሻሻለው የኢነርጂ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየተወያየ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ለ29 ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢነርጂ ፖሊሲ ከ 2013ዓም ጀምሮ የማሻሻያ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
ፖሊሲው አሁን ካለው አገራዊ አሁናዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ተሻሽሎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የ10 ዓመታት መሪ ዕቅድ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንደሚያስፈልጉ ገልፀው፤ በኢነርጂ ውም በመንግስትና በግል ዘርፍ ትብብር በማጠናከር አገራዊ እምርታ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ እንደተዘጋጀ ጠቅሰዋል።
በተለይም ዓለምን እየፈተነ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ የተጣጣመ ኢኮኖሚን ለማጎልበት እንደሚያግዝ፣ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ኢትዮጵያን በፖሊሲ አቅጣጫ የምትመራበት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ከረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅቶች በኋላ በርካታ ውይይቶች ተደርገው ወደመጨረሻ ደረጃ መሸጋገሩን ገልፀው፤ ተጨማሪ ግብዓቶች ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ ሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲፀድቅና ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ነው ያሉት።
የረቂቅ ፖሊሲው ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ጨምሮ ዘመናዊ እና አዳዲስ የኢነርጂ ዘርፎች ላይ ማተኮርንና ከውጭ የሚገባን ኃይል በአገር ውስጥ መተካት የሚል ይዘትም አካቷል።
የኢነርጂ ፖሊሲው ማሻሻል ምክንያቶች መካከልም ከአገር በቀል ኢኮኖሚ፣ ከአረንጓዴ ልማት፣ ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድና ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ማጣጣም በማስፈለጉ ነውም ተብሏል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥራትና አስተማማኝነት፣ የኃይል ብክነት ቅነሳ፣ በዘርፉ ጤናማ ፋይናንስ መፍጠር፣ ባህላዊ ባዮማስ አጠቃቀም ማስተካከል፣ የግልና የመንግስት ዘርፍ አጋርነት ማጠናከር፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና ቁጥጥር ማጎልበትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከረቂቁ ፖሊሲ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ተጠቅሰዋል።
በቀጣናው የኢነርጂ አቅምን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን ግኝትን ማሳደግም አንዱ የረቂቅ ፖሊሲው ግብ ነው።
ከኢነርጂ ዘርፎች መካከል አንዱ ኤሌክትሪክን በ10 ዓመት ውስጥ ህብረተሰቡን መቶ በመቶ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ እንደ ግብ ተቀምጧል።