የተጀመረውን የሰላም ሂደት በዘላቂነት ለማጽናት ሁሉም ወገን በቅንነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል - አባገዳ ጎበና ሆላ - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረውን የሰላም ሂደት በዘላቂነት ለማጽናት ሁሉም ወገን በቅንነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል - አባገዳ ጎበና ሆላ
አዲስ አበባ ህዳር 8/2015/ኢዜአ/ የተጀመረውን የሰላም ሂደት በዘላቂነት ለማጽናት ሁሉም ወገን በቅንነትና በኃላፊነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሐፊ እና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የፌደራል መንግስትና ህወሃት ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ መፈራረማቸው ይታወሳል።
የሰላም ስምምነቱ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱንና የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነዋል፡
ይህ የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን ሰላም የማይሹ ኃይሎችን ሴራ ያከሸፈና ለዘላቂ ሰላም ዕድል የሰጠ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሐፊ እና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ፤ ሰላም ለሰው ልጅና በምድር ላይ ላሉ ፍጥረታት ሁሉ መሰረታዊ ነገር ነው ብለዋል፡፡
" ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም" ያሉት አባገዳ ጎበና ሆላ ለሰላም መረጋገጥ ማንኛውንም ዋጋ መክፈል እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መንግስት እየሄደበት ያለውን ሂደት አድንቀው፤ ችግሮችን በንግግርና በምክክር ለመፍታት የሄደበት ርቀት የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አባገዳ ጎበና ሆላ አክለውም የተጀመረውን የሰላም ሂደት ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቅንነትና በኃላፊነት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀገር መሪዎች በሰላም ማፅናት ሂደቱ ሚናቸው የላቀ መሆኑንም አንዲሁ፡፡
የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል እና የታሪክ ምዕራፍ መጀመር ወሳኝ ሚና እንዳለው በተለያዩ ጊዜያት ተጠቆሟል፡፡