በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተግባራዊ በተደረገው የተማሪ ተኮር የትምህርት አቀራረብ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተግባራዊ በተደረገው የተማሪ ተኮር የትምህርት አቀራረብ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 7 ቀን 2015 በኢትዮጵያ በሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የተማሪ ተኮር የትምህርት አቀራረብ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተገለጸ።
ከፕሮጀክቱ ትግበራ የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር ወደ ሌሎች መጠለያ ጣቢያዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።
'ፕላን ኢንተርናሽናል' በተሰኘው ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት አዘጋጅነት "ፕላይ ማተርስ" ፕሮጀክት ትግበራ ሂደትና አፈጻጸም ላይ ያተኮረና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
"ፕላይ ማተርስ" ፕሮጀክት ዓላማው በስደተኞች መጠለያና ማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን በቀላል ዘዴ እውቀት እንዲጨብጡ ማስቻል ነው።
ፕሮጀክቱ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እና የአካባቢውን ህብረተሰብ ልጆች ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ይዞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱ በስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ተማሪዎች ቀላል፣ አዝናኝና ጨዋታ የታከለበት የመማር ማስተማር ዘዴን በማካተት ሲሆን ስልጠናውም መምህራንን፣ ወላጆችና እንክብካቤ አድራጊዎችን ያካትታል።
ፕሮጀክቱ በተማሪ ተኮር የመማር ማስተማር ስነ-ዘዴ ከ3 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ተማሪዎች ተፈላጊውን ክህሎት እና የአዕምሮ ዕድገት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ማስቻል ነው።
ተማሪ ተኮር የትምህርት አቀራረብ ትግበራ በኢትዮጵያ በሚፈለገው ደረጃ ባለመድረሱ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ በመድረኩ ላይ ተነስቷል።
የፕላን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሙዳሰር ሲዲቂ እንደገለጹት፤ የፕሮጀክቱ ትግበራ ሁለት ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተደራሽ አድርጓል።
ተማሪዎችን በቀላል ዘዴ ለማስተማር የሚያግዙ የትምህርት መርጃ መሳሪዎች ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች መሰራጨቱን፤ ከ2 ሺህ በላይ አስተማሪዎችና አሰልጣኞችም ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ደስታ፤ በርካታ ስደተኞችን ባስጠለለችው ኢትዮጵያ ለትምህርት የደረሱ ህጻናት 393 ሺህ 325 ህጻናት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን በሙሉ በትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የመንግስትን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኦሞድ፤ 'ፕለይማተርስ' ፕሮጀክት ከመንግስት ትውልድ ቀረጻ ስራዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ጥራት ያለው ትምህርትን ለህጻናት ተደራሽ ለማድረግ እና ስብዕና ለመቅረጽ ሁነኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ ሚኒስቴሩም የፕሮጀክቱ ተሞክሮ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ትምህርትና አመራሮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉቀን ንጋቱ በበኩላቸው፤ በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ታዳጊዎች ከመጡበት እና ካሉበት አገር ሁኔታ መለያየት አንጻር አዕምሯዊ ጫናዎች ይዳረጋሉ።
በአምስት ዓመቱ የፕሮጀክቱ ትግበራ መጠለያ ጣቢያዎች እና በአካባቢው በሚገኙ ህብረተሰብ ክፍሎች እስከ 800 ሺህ ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ግብ መቀመጡን ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴሩ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው አካባቢዎች የተገኘውን ልምድ ወደ ሌሎች ክልሎች ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።