ቀጥታ፡

የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ በአዲስ መልክ የፍላጎት መግለጫ ወጣ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 7 ቀን 2015 የገንዘብ ሚኒስቴር የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ በአዲስ መልክ የአንድ ወር ፍላጎት መግለጫ ማውጣቱን ገለጸ።

የሶስተኛው የቴሌኮም ፍቃድ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለመጀመር የሚያስችል ምክክር ዛሬ መጀመሩን አመልክቷል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ተቋርጦ የነበረውን 40 በመቶ የቴሌኮም ድርሻ የመሸጥ ሂደትን እና ሶስተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ መስጠት በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በመግለጫቸው፣ 40 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ለመሸጥ የተጀመሩ ሂደቶች እንደነበሩ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፍ የማክሮ ኢኮኖሚው መቀዛቀዝና በሀገር ውስጥ በነበረው የሰላም እጦት ሳቢያ ሂደቱ ተቋርጦ ቆይቷል ብለዋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እየተለወጡ መምጣታቸው፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ (ማክሮ ኢኮኖሚ) መረጋጋት በማሳየቱና የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ካለው ምቹ ሁኔታ አንጻር የኩባንያው ድርሻ የመሸጥ ሂደት እንዲጀመር መደረጉን አመልክተዋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የፍላጎት መግለጫ ማውጣቱን ጠቁመዋል።

በሽያጩ ለመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ሚኒስቴሩ በድረ-ገጹ ላይ ባወጣው የፍላጎት ማሳወቂያ ቅጽ ፍላጎታቸውን እንዲያሳውቁ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አጠቃላይ ሂደቱን የሚያሳይ ዝርዝር መረጃም በተቋሙ ድረ-ገጽ በኩል ይፋ እንደሚደረግ አክለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያው ዘርፉን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ክፍት የሚያደርግና የኢትዮ ቴሌኮም የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ሶስተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ ለመስጠት ፍላጎቶች የታዩ በመሆኑ ሂደቱ እንደሚጀመር ጨምረው ገልጸዋል፡፡   

ለቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ የመስጠት ስልጣን ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን ነው፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ፈቃድ ለማግኘት ፍላጎት ያላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከተቋሙ ጋር መወያያትና መመካከር እንደሚችሉና ለዚህም የሚረዳ የምክክር ሰነድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ በከፊል ወደ ግል የማዘዋወር ሂደት ኩባንያው አብዛኛውን ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

መቀመጫውን በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ያደረገው ዴሎይቴ የተሰኘ ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያ ሽያጩን አስመልክቶ የማማከር ሥራ ያከናውናል።

መንግስት ኢትዮ ቴሌኮምን እንደ አንድ የቴሌኮም ፈቃድ የወሰደ ኩባንያ በመቁጠር በጊዜያዊነት በኢትዮጵያ ሶስት የቴሌኮም ብቻ ፈቃድ እንዲሰጥ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ቮዳኮም፣ ሳፋሪኮም፣ ቮዳፎን፣ ሲሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች በስሩ የያዘው 'ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ' ዓለም አቀፍ ጨረታ በማሸነፍ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም