በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው - የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው - የምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 7/2015 በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው ለመመለስም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደትም ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በማገዝ ወደ ቀደመ የኑሮ እንቅስቃሴቸው እንዲመለሱም ኢትዮጵያዊያን የሚችሉትን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆኗን አብራርተዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተስፋ ሰጪውን ኢኮኖሚ በተሰማራበት መስክ መደገፍና በጦርነቱም ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ማገዝ ወገናዊ ኃላፊነት መሆኑን አውቆ ለተግባራዊነቱ መትጋት አለበት ብለዋል።
የምክር ቤት አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደገለጹትም ኢትዮጵያ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ጫና ሳትበገር ተሻጋሪና ውጤታማ የልማት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ገልጸዋል።
የአገልግሎት፣ የግብርናና ሌሎች ዘርፎችም ለኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት የጣሉ ተጨባጭ ስኬቶች የተገኙባቸው መስኮች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
መንግስትም ጦርነትን በሰላም በመቋጨት የአገርን ሉዓላዊ አንድነት ለማስቀጠል የሄደበት ርቀትም የሚመሰገን መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሄ ምላሽ ለመስጠት በተከተለችው መርህ የገዘፈ ውጤት ማምጣት መቻሏን ጠቁመዋል።
ሰላም የኢትዮጵያ ህዝብ ጽኑ ፍላጎት በመሆኑም የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለኢኮኖሚያዊ እድገትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት የሚጥል መሆኑን አመላክተዋል።
በምክር ቤቱ አባላት በኩልም የህዝብን የሰላም ፍላጎት በመደገፍ መስራት እና ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነትም በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ዑስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ የሰላም ስምምነቱ በጦርነት ቀጠና የነበረው ህዝብ ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች ለመቋጨት የላቀ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።
መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት "መደገፍ፣ መገንባት እና ማቋቋም" በሚል መርህ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በሂደቱም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እና ለመደገፍ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የሰላም እጦት የማህበረሰቡ ከፍተኛ ጭንቀት ነበር ያሉት የምክር ቤት አባሉ፤ ሰላም ከሌለ እድገትም ሆነ ወጥቶ መግባት ችግር የሚሆንበትና የአገር ኢኮኖሚም የሚቀጭጭበት ነው ብለዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የተደረሰው የሰላም ስምምነትም ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ ግንዛቤ የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱም ትልቅ ውሳኔና ኢትዮጵያንም ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግር እንደሆነ ገልጸዋል።