ቀጥታ፡

እውነት በክፋትና በሴራ ብትሸፈንም በዘላቂነት ልትቀበር አንደማትችል ከመስቀሉ ልንማር ይገባል - ጠ/ሚ ዓብይ አህመድ

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 "በዓለ መስቀል እውነት የቱንም ያህል ዘመን፣ በምንም ያህል ውሸትና ቅጥፈት፣ ተንኮልና ሤራ፣ በየትኛውም ስልጣንና ክፋት ብትሸፈንም በዘላቂነት ልትቀበር እንደማትችል አይነተኛ ማሳያ ነው" ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚከበረውን የደመራና መስቀል በዓል በማስመልከት ለክርስትና እምነት ተከታዮችና ኢትዮጵያዊያን የእንኳን አደረሳቸሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። "ለዘመናት ተቀብሮ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተጫነው ተራራ-ከተደበቀበት ስውር ስፍራ፣ በክፋት ከተተወበት ምሽግ ጎራ ይወጣ ዘንድ በአማናዊ ደመራ-ሰማያዊ ምልክት የታየበትን ቀን ለምናከብርበት ለዚህ በዓል ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ የእንኳን አደረሳችሁ" በማለት። መስቀል የክርስትና እምነት ተከታዮች ታላቅና ግሩም በዓል ቢሆንም ቅሉ ክብሩና ሀብትነቱ ግን የመላ ኢትዮጵያዊያን ጸጋ ነው ያሉት ዶክተር ዓብይ "ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቱና ከመንፈሳዊ እውነትነቱም ባሻገር እውነትን ለዘመናት በውሸት፣ ተንኮል፣ ሴራ፣ ክፋት ብትሸፈንም በዘላቂነት መቅበር እንደማይቻል ከመስቀሉ መማር ይኖርብናል" ብለዋል። "ለጥቂት ጊዜ ፀሐይን እንደሚሸፍን ደመና እውነትን ለተወሰነ ጊዜ መከለል፣ ውሸትንም እውነት ማስመሰል ይቻል ይሆናል እንጂ እውነት ማሸነፏና ከተቀበረችበት ወጥታም እንደምታሳፍር የክርስቶስ መስቀል ታሪክ ግሩም ማስረገጫ ነው" ብለዋል ዶክተር ዓብይ። "የከበራ ሥርዓቱን ቀደምት አበውና እመውም ጭምር በሆነው የበዓል ስርዓታችን የመስቀሉን አስተርእዮ ሁለንተናዊ መልክ በቀጥታ የተረኩልን፤ በጥበብም ያቆዩልን ቢሆንም በተራዛሚው ግን የማይታወቅ የተሰወረ፤ የማይገለጥ የተከደነ ነገር ለዘለአለም ሊኖር አለመቻሉን መንፈሳዊና ሰዋዊ እውነት በድንቅ የበዓል ክዋኔ ሂደት አቆይተውልናል" ብለዋል። በዚህም ለእውነት ብቻ እንድንቆም፤ ለጊዜያዊ ጥቅም ስንል እውነትን እንዳንቀብር፤ ሥልጣን አለን-ብንናገር እንሰማለን- ጊዜው የእኛ ነው በሚል ቀባሪና አደናጋሪ አተያይ እውነትን ብንቀብራት "እውነት ያው እውነት ናትና ጊዜዋን ጠብቃ እንደምትወጣ፤ በተለየ ክብርና በድንቅ የመገለጥ ምስጢር እንደምትነሳ እንድናስብ የሚያደርገንን ይሄንን ታሪክ በመሳጭ የከበራ ጥበብ አደረጅተው እዚህ አድርሰውልናል" ሲሉም ገልጸውታል። "በዙሪያችን ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ ስም ማጥፋቶች፣ የሐሰት ወሬዎች፣ አሳሳች አሉባልታዎች እና በስሜት የሚነዱ ማስመሰሎች በገፍ አሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እነዚህ ሁሉ ጊዜያዊ ግርግሮች ለጊዜያዊ መሸንገል እንጂ ለዘላቂ ድል መሰረት ሊሆኑ እንደማይችሉ የመስቀሉ ታሪክ ሁነኛ ምሳሌ ነው" ብለዋል። ምንም ያህል ቢያብረቀርቁ በፍጹም ወርቅ እንዳልሆኑ መገንዘብ እና እውነተኛው ወርቅ ግን ጊዜውን ጠብቆ እንደሚወጣ ከመስቀሉ ታሪክ እንማር ዘንድ ይገባናልም ነው ያሉት። "ከጸናን፣ ካልተከፋፈልን፣ መድረሻችንን ካወቅን፣ ከበደል ሳይሆን ከፍትህ ካበርንና ለሐሰተኞች ጆሮ ልቦናችንን ከነፈግን እውነት ብትቀበር እንኳን እንደ ታላቁ መስቀል ሁሉ ቢዘገይም ነጻ እናወጣታለን፤ ነጻ ማውጣትም ብቻ ሳይሆን ሰማየ ሰማያት ደርሶ የመገኛ አቅጣጫ ብስራት ይዞ የተመለሰ ጭስ እንዳስገኘው ደመራ በዓለም ፊት እናበራታለን- እናደምቃታለን።" ነው ያሉት። "የደመራ በዓል የመደመር በዓል ነው ልንለውም እንችላለን፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ እንጨት ተደምሮ ችቦ በመስራት ታላቁን ደመራ ይሰራል" ሲሉም አክለዋል። "እያንዳንዱ እንጨት ተደምሮ ታላቅ ደመራ የሚሆነው እየተጨፈለቀ ሳይሆን ህብር በራሱ ብርሀን እየደመቀ፤ እየተዋጠ ሳይሆን የራሱን ብርሀን እየሰጠ፤ እየተጠፋፋ ሳይሆን አንዱ በአንዱ ውስጥ እየሰፋ፤ እየተጨመረ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ። ደመራ ደመራ እንዲሆን እያንዳንዱ እንጨት ሲቀጥል ችቦ በአንድነት ለአንድ ዓላማ በጥበብና በውበት ተደምሮ እንዲቆም አንዱ ከሌላው መያያዝ ግዴታ እንጂ ሲሻ ብቻ የሚሆን ውዴታ አይደለም። "መያያዝ፣ ህብር መፍጠር፣ አብሮ መቆምና አብሮ ማብራት ለደመራ ባህሪው ሳይሆን ተፈጥሮው ነው፤ እኛም እንዲያ ነን ደመራነት ነው የሚያምርብን፣ የሚያበረታን፣ የሚያቆመን፣ የሚያበራን፣ የሚያደምቀን እና የሚያሞቀን" ብለዋል። "የሺ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ" እንደሚባለው እንጨቶቹ በልጥ ተያይዘው አንድ ችቦ እንደሆኑት ሁሉ ማያያዣ ልጡ ሕጋችን፣ ሥርዓታችን፣ እሴቶቻችን፣ ለውጥ ፈላጊነታችን፣ መፈቃቀዳችንና መተባበራችን ምሳሌ መሆን አለበት። ችቦዎቹ በተናጠል ደመራ መመስረት ስለማይችሉ በአንድ ዋልታ ዙሪያ መቆም አለባቸው፤ እኛም ለየብቻ እንወድቃለን፣ በጋራ እንቆማለን እና በኢትዮጵያዊነታችን ዋልታ ስር መሰባሰብ አለብን፤ ሁላችንም የምንቆምበትና የምንቆምለት አገራዊ እሴትና ማንነት፣ አገራዊ አንድነትና መንግሥት ስላለን ሁላችንም ልንደመር ይገባል ብለዋል። "አገራችን ሁላችንም ተደምረን የምንቆምላትና የምንቆምባት፤ ለአንድ አገራዊ ዓላማ የምንሰለፍባት "ደመራ" በመሆኗ በየትኛውም ቦታ ደመራ ስትመለከቱ ኢትዮጵያን አስቡ፤ ራሳችሁን ከችቦው ውስጥ ፈልጉ፤ ችቦው እንዲቆም፣ ደመራው እንዲጸና እኔ ምን አድርጌያለሁ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ። በኢትዮጵያዊያን ባህል ከመስቀል ወዲያ ክረምት፣ ረሐብና ችጋር የለም፤ ክረምት የሚያመጣው ፈተና ከደመራ በኋላ ያልፋል ተብሎ ይታመናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። "መከራን፣ ችጋርን፣ ጦርነትንና ግጭትን በበቂ ሁኔታ ቀምሰናቸዋል፤ አይናፍቁንም፤ አንመኛቸውም፤ አሁን እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ደመራው ሁሉ አንድ ሆነን ተደምረናልና ከዚህ በኋላ እነዚያ የእንባ ሰበቦቻችን አይቀጥሉም፤ እንዲቀጥሉም አንፈቅድም።" አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነው ሊፍጨረጨሩ ይችላሉ፤ ከመስቀል በኋላ እንደሚመጣ ዝናብ ነው፤ ዝናቡም እያለቀ፤ ችግሩም እየነጠፈ ይሄዳል እንጂ እድሜ አይኖራቸውም።" ነው ያሉት። ይህ እውን እንዲሆን ግን ደመራው በሚለኮስበት ቅጽበት እንደ አገር በመደመር ሁላችንም የበኩላችንን ለማድረግ ቃልኪዳናችን እናጽና ሲሉም ጠይቀዋል። "መስቀል አዲሱ እህል እሸት የሚበላበት የአርሶ አደሩ ተሥፋ በመሆኑ ተሥፋውን ማማ ሠርቶ ከአውሬ እንደሚጠብቅ ሁሉ እኛም የዴሞክራሲን፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ የመደመርና የለውጥን ተሥፋ እየቀመስን ተስፋችንን የአንድነት ማማ ሰርተን ከአውሬዎችና ከአጥፊዎች ልንጠብቅ ይገባል" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። "ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!" ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!" ሲሉም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም