17ኛው የብሔረሰቦች ቀን በሶማሌ ክልል ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
17ኛው የብሔረሰቦች ቀን በሶማሌ ክልል ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል
ጅግጅጋ (ኢዜአ) ህዳር 7 ቀን 2015 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሶማሌ ክልል ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ኢብራሂም ሀሰን አስታወቁ።
አፈ-ጉባኤው በዓሉ የኢትየጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሠነድ የሆነው ህገ-መንግስታችን በተለይም ለሶማሌ ህዝብ ያስገኛቸውን ቱርፋት በመዘከር ይከበራል ብለዋል።
ለበዓሉ ስኬታማነት በክልል ደረጃ የተለያዩ አካላትን ያካተተ አብይ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅሰው፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዘጋጀውን የ17ኛ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ቀን አከባበር መሪ እቅድን መሰረት በማድረግ ክልሉ እቅድ አሰናድቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
የሶማሌ ህዝብ በፌዴራሊዝም ስርዓቱና ህገ-መንግስቱ የተረጋገጡለትን ዲሞክራሲያዊና ሠብዓዊ መብቶች "ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ ሃሳብ በዓሉ በመጪው ሰኞ በፓናል ውይይት ማክበር እንደሚጀመር አስረድተዋል።
ምክትል አፈ-ጉባኤው አንዳሉት በፓናል ውይይቱ ላይ የሶማሌ ክልልን የኢኮኖሚና ፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታን፣ በክልሉ የተዘረጉ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ የቱሪስት መስህቦችንና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ይቀርባሉ።
እንዲሁም በዓሉ በደም ልገሳ እና በአጎራባች የሶማሌና የኦሮሚያ ወረዳዎች መካከል ዕለቱን በጋራ በማክበር አንድነታቸውን ለማጠናከር መመቻቸቱንም ገልጸዋል።
የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ለህዝቦች እያስገኘ ያለውን ጠቀሜታዎች እና የህዝብ ለህዝብ ትስስራቸውን በሚያጠናክሩ ፕሮግራሞች ጭምር ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በዓሉ ከህዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልል ደረጃ በጅግጅጋ ቀጥሎም በተዋረድም እስከ ወረዳዎች ድረስ በተለያዩ መሰናዶዎች እንደሚከበር አመልክተዋል።
ክልሉን በመወከል ደግሞ በፌደራል ደረጃ በዓሉ ወደ ተዘጋጀበት ሀዋሳ ከተማ 25 አባላት ያሉት የባህል ቡድን መሸኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
ቡድኑ በ17ኛ የብሔረሰቦች ቀን ላይ ዝግጅቶቹን በማቅረብ ክልሉን ለሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር ይበልጥ በማስተዋወቅና ትስስር በማጠናከር ለበዓሉ ድምቀት የድርሻውን እንዲወጣ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።