መንግስት ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት የበኩላችንን እንወጣለን -የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለዘላቂ ሰላምና ዕድገት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት የበኩላችንን እንወጣለን -የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች
ጂንካ (ኢዜአ) ህዳር 7 ቀን 2015 መንግስት ለዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት እያከናወናቸው ላሉ ሥራዎች የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትናንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ መንግስት የሰላም ስምምነቱ እንዲጸና የሄደበትን ርቀት አድንቀዋል።
ችግርን ተቋቁማ ማለፍ የምትችል ኢትዮጵያን ለመገንባት ቂምና ቁርሾን በመተው ሀገራዊ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባም ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ የህዝቦች አብሮነትንና ልማትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚንቀሳቀሱም ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ራሔል ታደሰ ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተግባር መታየቱን ጠቁመዋል።
"መንግስት አስቀድሞ የሰላም አማራጭን በማስቀመጥ በቅርቡም ከህወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱ ለህዝብና ለሀገር ሰላም ሲል የሄደበትን ርቀት ያሳያል" ብለዋል።
በተለይ የህዝብን አብሮነት ለማይፈልጉ አካላት መጠቀሚያ ባለመሆን አብሮነትና ልማትን በማጠናከር ድህነትን ለማሸነፍ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ከትናንቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግርም መንግስት በእጅ ያሉ ጸጋዎች ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት የሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን እንደተረዱ ገልጸዋል።
"ሁላችንም ከጦርነቱ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ ወጥተን አንድነትና ልማት ላይ ልናተኩር ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ የሱፍ አሊ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት ሲባል በመንግስት የተሄደውን ርቀት በተመለከተ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በብዙ መስዋዕትነት ለመጣው የሰላም ስምምነት ስኬታማነት ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም አቶ የሱፍ አረጋግጠዋል።
የተገኘው የሰላም አየር ዘላቂ እንዲሆን የህዝቦችን አንድነት በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ አተኩረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
"ለችግር የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በመንግስት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተረድቺያለሁ" ያሉት ደግሞ ወይዘሪት ይመኙሻል ተፈሪ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
ከሰላም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ አትራፊ መሆናቸውን በመረዳት የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረሱ የሰላም ዋጋ ተገቢ ትኩረት ማግኘቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የሰላም ስምምነቱ ለሁሉም መልካም ዕድል መሆኑንና ሀገርን ከፍ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ነዋሪዋ፣ ለስኬታማነቱ ከመንግስት ጎን እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።