ባንኩ የሶስተኛ ደረጃ ህክምና ለሚሰጡ የጤና ተቋማት ብድር መስጠት ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ የሶስተኛ ደረጃ ህክምና ለሚሰጡ የጤና ተቋማት ብድር መስጠት ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 7 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁና በውጭ አገራት የሚሰጡ የሶስተኛ ደረጃ የህክምና አገልግሎቶችን በአገር ውስጥ መስጠት ለሚችሉ የጤና ተቋማት ብድር መስጠት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
ሶስተኛ ደረጃ (ተርሸሪ ሌቭል) ሆስፒታል ዘመናዊ መሳሪያዎችን አካቶ የተሟላ አገልግሎትን ለታካሚዎች የሚሰጥ ሲሆን ከሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ሆስፒታሎች በሪፈር የሚላኩ ታካሚዎችን ተቀብሎ አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ተቋም ነው።
ባንኩ ከዚህ ቀደም ይስተዋልበት የነበረውን የተበላሸ ብድር ምጣኔ ወደ ጤናማነት ለማምጣት በርካታ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
አሰራሩን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ ባንኩ ካከናወናቸው የለውጥ ተግባራት መካከል የባንኩ የማበደርና ብድር የማስመለስ ምጣኔ ከአመት አመት መሻሻል እያሳየ ይገኛል።
ባንኩ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ከማድረግ ባሻገር አዳዲስ አሰራሮችን እየተገበረ ሲሆን የፈጠራ ሃሳብ ላላቸውን ሰዎች ብድር መስጠት በቅርቡ ከጀመራቸው መካከል ይጠቀሳል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት ባንኩ የገቢ ንግድን በሚተኩና የወጭ ንግድን በሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በአሁን ሰዓትም በርካታ ገንዘብ የሚጠይቁና በውጭ የሚደረጉ የህክምና አገልግሎቶች በአገር ውስጥ እንዲጀመሩ ለማስቻል የሶስተኛ ደረጃ ህክምና የሚሰጡ ተቋማትን ለመደገፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በዘርፉ ድጋፍ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረቡ መኖራቸውን አንስተው ፕሮጀክቱን በቀጣዮቹ አራት ወራት ለማፅደቅ መታቀዱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ባንኩ የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ፕሮጀከቶችን ለመደገፍ አቅዶ ስራ መጀመሩን አንስተዋል።
በሁሉም ክልሎች 90 ፕሮጀክቶች በሙከራ ደረጃ ለመተግበር ስራ መጀመሩን በማንሳት።