ቀጥታ፡

መንግስት ያቀረበልን አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ከከፋ ችግር ታድጎናል -የራያ ባላ ወረዳና አካባቢው ነዋሪዎች

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 7/2015 መንግስት ያቀረበልን አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ከከፋ ችግር ታድጎናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የራያ ባላ ወረዳና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አከባቢዎች መካከል ራያ ባላ ወረዳ ተጠቃሽ ነው።

ኢዜአ በወረዳው ተገኝቶ ከ5 ሺህ በላይ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ መቀበላቸውን ታዝቧል።

የሰብዓዊ እርዳታ ተጠቃሚዎች እንዳሉትም ጦርነቱ መቆሙን ተከትሎ  መንግስት ተደራሽ ባደረገው ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።

ሰብዓዊ ርዳታ ከቀረበላቸው መካከል ለምለም ዕቁዋርኪሮስ እና ሃፍተ ዋሲሁን በከፋ ችግር ውስጥ እንደነበሩ ገልፀው፤ በተደረገላቸው ድጋፍ እፎይታ እንዳገኙ ገልጸዋል።

በዚህም በጊዜያዊነት ተጠልለውበት ከቆዩበት ጃራ ስደተኞች መጠለያ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልፀው፤  መንግስት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን አድንቀዋል።

ኢዜአ በስፍራው ተገኝቶ እንደታዘበውም በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በጦርነቱ ወደተጎዱ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ነው።

This image has an empty alt attribute; its file name is 555555-1-1024x692.png

ከጭነት አሽከርካሪዎች መካከልም አቶ ውብሸት ደምሴ እንዳሉት አሁን ላይ ሰብዓዊ ርዳታን በአግባቡና በፍጥነት ተደራሽ  ለማድረግ  አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል።

የራያ ባላ ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ተካ ተበጀ እስካሁን ባለው ሂደት 6 ሺህ 800 ኩንታል ሰብዓዊ እርዳታ በጦርነት ለተጎዱ የወረዳው ነዋሪዎችና ተፈናቃዮች መከፋፈሉን አንስተዋል።

ያም ሆኖ አካባቢው በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዳ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች ለሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፍ የማጓጓዝ ስራዎች የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት ክፍት ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በተጨማሪ መንግስት በጦርነት ጉዳት ወደ ደረሰባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እያደረገ ስለመሆኑ አሳውቋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫም  ከሰላም ስምምነቱ ማግስት ጀምሮ ከ43 ሺህ 200 ኩንታል በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ  በራያ ባላ፣ ኮረም እና አላማጣ አካባቢዎች መሰራጨቱን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም