ቀጥታ፡

ከውጭ የሚገባውን የዱረም ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 07 ቀን 2015 ከውጭ የሚገባውን የዱረም ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳኘ ሞጆ፤ በተለምዶ የቅንጨ ስንዴ የሚባለው የዱረም ስንዴ ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችው ዝርያ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

የዱረም ስንዴ በኢትዮጵያ ቢመረትም መንግስት ለፓስታና መኮረኒ ፋብሪካዎች ምርቱን ከውጭ እንዲያስገቡ ድጎማ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህም አርሶ አደሩ ላመረተው ምርት ገበያ ከማጣቱም በላይ ኢትዮጵያን ለውጭ ምንዛሬ ወጪ ዳርጓት መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡

መንግስት ከውጭ ሲገባ የቆየውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት እንዲሸፈን በማድረጉ የአርሶ አደሮች ምርት ወደ ገበያ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከልም ለቆላና ደጋማ ስነ-ምህዳር የሚስማሙ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማፍለቅ ምርትና ምርታማነቱን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ የዱረም ስንዴ ካመረተ በኋላ የሚረከበው አካል እንደሚያስፈልገው የገለጹት ዶክተር ዳኘ፤ ከዚህ አኳያ ምቹ የሆነ የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እንደ ባሌ፣ አዳአ ያሉ አካባቢዎች ከዳቦ ስንዴ በተጨማሪ ለዱረም ስንዴ ምርትም ተስማሚ  መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ማዕከሉ ለአካባቢው ስነ-ምህዳር የሚመቹ የስንዴ ዝርያዎችን እያላመደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከውጭ የሚገባውን ምርት ከማስቀረት ባለፈ የዱረም ስንዴን ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ፈጥረናል ብለዋል፡፡

በማዕከሉ የዱረም ስንዴ ብሔራዊ አስተባባሪ ዶክተር ሽታዬ ሆማ፤ መንግስት የዱረም ስንዴ ከውጭ እንዳይገባ ማድረጉ በምርምር ያገኘነው ቴክኖሎጂ በስፋት ስራ ላይ እንዲውል እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በዚህም ከውጭ የሚገባውን የዱረም ስንዴ በአርሶ አደሩ ምርት በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ብሎም የምርምር ውጤቶች አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ፤ የዱረም ስንዴ እንደ ዳቦ ስንዴ ሁሉ በማንኛውም የአየር ንብረትና ወቅት መልማት እንደሚችል አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከአሁን በፊት የተጀመረውን የዱረም ስንዴ ምርት እንቅስቃሴ በማስፋት ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም