በመዲናዋ 10 ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት የተጀመረው እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 በአዲስ አበባ ከተማ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ 10 ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶችን ለመገንባት የተጀመረው እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

14ኛው 20/80 እንዲሁም 3ኛው 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሥነ ስርዓት ዛሬ መከናወኑ ይታወሳል።

የከተማው ህዝብ ዋነኛ ጥያቄ የሆነውን የቤት ችግር ለማቃለል ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮችን ገቢራዊ እያደረገ ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ከዚህ አኳያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡    

ለአብነትም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እየተካሄደ ያለው የ10 ሺህ ተገጣጣሚ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።  

እንደ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጻ፤ የመኖሪያ ቤት ችግሩን ለመፍታት የግልና የመንግስት አጋርነት አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም