17ኛውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቋል--የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር

173

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 -17ኛውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በተሳካ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጉባኤውን አስመልክቶ ከተቋቋመው የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት ጉባኤው ከህዳር 19 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው ኢንተርኔት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሀሳቦች የሚነሱበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በጉባኤው የሚመነጩ ሀሳቦች ለፖሊሲ አውጭዎች እና ለውሳኔ ሰጭ አካላት በግብዓትነት እንደሚውሉም ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተሞክሮ ለመቅሰም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ጉባኤውን ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል፡፡

ከጉባኤው በተጓዳኝ በመዲናዋ የተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጉብኝት እና ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ፌስቲቫሎች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል፡፡

ለጉባኤው ስኬትም የተለያዩ አካላት በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደተለመደው እንግዳ ተቀባይነታቸውን በተግባር አንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።

በጉባኤው ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ከ 2 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም