ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሕዳሴ ለማስቀጠል ወጣቶች በአርበኝነት ስሜት ሊያገለግሉ ይገባል - የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 የኢትዮያን የህዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል ወጣቶች በአርበኝነት ስሜት አገራቸውን ማገልገል እንዳለባቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ አስገነዘቡ። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ሠላም የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት አሁን ላይ በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ የሚያበላሹ ናቸው። ለረጅም ዓመታት በመቻቻል ይኖሩ የነበሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በትንንሽ ምክንያቶች ግጭት ውስጥ ሲገቡና የሰው ህይወትና ንብረት ሲጠፋ ማየት የፈጠረባቸውን ሀዘንም ገልጸዋል። አገራዊ አንድነትን ለማምጣትና ወጣቶችን ከጥፋት ለመታደግ የአገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል የቀድሞው ፕሬዚዳንት።  የአገር ሽማግሌዎች በተዘጋጀላቸው አዳራሽ በሠላም ጉዳይ ከየትኛውም አካባቢ መጥተው መምከር ይችላሉም ብለዋል። ወጣቶች ወደ ግጭት እንዳይገቡ መምከርና መገሰጽ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ነው የተናገሩት። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሠላም እንዲፈጠር በፕሬዚዳንትነት ጊዜያቸው ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርና አሁን በአገራቱ መካከል የተፈጠረው እርቅ ካሰቡት ጊዜ የፈጠነ መሆኑን ገልጸዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ስለ መጪው የኢትዮጵያ ዕድገት  ሲተነብዩ ። ''95 ሊሆነኝ ነው በጣም ደስተኛ ነኝ። ውጪ አገር ያሉትም፣ ተቃዋሚዎችም፣ ደጋፊዎችም በሙሉ አገራቸውን ለመርዳትና ከአገራቻው ጋር ለመሆን ያሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዳሴ ነው በጣም ደስ ይላል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በጣም ትልቅ ሰው ነው፣ ፈጣን ሰው ነው፣ አስተያየቱም ሰፊ ነው፣ ዳያስፖራውም መጥቷል እዚህ እኛ አገር ያለውም ይሰራል። ኢትዮጵያ ወደ ፊት ደሃ የማትባልና ወደኋላ የቀረች አገር የማትባል ነው የምትሆነው ሲሉ ተናግረዋል። የ95 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው አገሪቷ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ለዜጎቿ ምቹ እንደምትሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም