ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ አለም አቀፉን የሳይንስ፣ ምህንድስናና ህክምና አካዳሚ(ኢያፕን) በጥምር ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመረጡ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ አለም አቀፉን የሳይንስ፣ ምህንድስናና ህክምና አካዳሚ(ኢያፕን) በጥምር ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመረጡ
ህዳር 06/2015(ኢዜአ) ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ አለም አቀፉን የሳይንስ፣ ምህንድስናና ህክምና ኢንተር አካዳሚ ፓርትነርሺፕ (ኢያፕን) በጥምር ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በአሪዞና በተካሄደ የዘርፉ ጉባኤ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ በሳይንሱ ዘርፍ ግዙፍ የሆነውን አለም አቀፍ ተቋም እንዲመሩ መመረጣቸውን ገልጿል።
አካዳሚው ለፕሮፌሰሩ ባስተላለፈው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ፕሮፌሰር ማስረሻ አለም አቀፉን የሳይንስ፣ ምህንድስናና ህክምና ኢንተር አካዳሚ ፓርትነርሺፕ (ኢያፕን) በጥምር ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸውን ገልጿል።
ፕሮፌሰር ማስረሻ ተቋሙን ከአሜሪካዊቷ ተመራማሪ ዶክተር ማርጋሬት ሃምበርግ ጋር እንደሚመሩ ነው በመረጃው የተመለከተው።
ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ደረጃ በስነ ምህዳርና ስነ ሕይወት ዘርፎች ዙሪያ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱና ተቋማትን በማቋቋም ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተገልጿል።
የዕጽዋት ስነ ምህዳር ባለሙያው ፕሮፌሰር ማስረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም አመታት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን እ.አ.አ በ1990 ከጀርመኑ ዳርማስታዳት ዩኒቨርሰቲ በዕጽዋት ስነምህዳር ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በ2002 ደግሞ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተቀበሉት ፕሮፌሰር ማስረሻ በስነ ሕይወት፣ ዕጽዋት፣ በአካባቢያዊ ስነ ምህዳርና ተያያዥ ዘርፎች ከፍተኛ ምርምሮችን አካሂደዋል።