ቅርሶች በስጦታ እቃዎች ስም ለህገ ወጥ ዝውውር እየተጋለጡ ነው - የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ቅርሶች በስጦታ እቃዎች ስም ለህገ ወጥ ዝውውር እየተጋለጡ ነው - የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 በኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶች በስጦታ እቃዎች ስም ለህገ ወጥ ቅርስ ዝውውር እየተጋለጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
"ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውር መከላከል ቀን" በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ3ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶች ለህገ ወጥ ዝውውር እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ህብረተሰቡ፣ የፍትህ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
ቅርሶች በባህላዊ ስጦታ እቃዎች ስም ላልተገባ ተግባርና ለዝርፊያ እየተጋለጡ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ በቅርሶች ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከመዘረፋቸው በተጨማሪ የቅርስ ግንዛቤ በሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም በሌሎች የፍተሻ ጣቢያዎች የሚመደቡ የፍተሻ ባለሙያዎች የቅርስ እውቀት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
መንግስት ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከልና ህብረተሰቡ ስለ ቅርስ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ አሰራር ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ አበባው፤ ቅርሶችን በአግባቡ የመመዝገብ ስራው በሚፈለገው ልክ አለመሆኑ ህገ ወጥ ዝውውሩን አባብሶታል ብለዋል፡፡
ባለስልጣኑ ህገ ወጥ የቅርሶች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዲጂታል በሆነ መንገድ ለማደራጀትና ለማልማት ስራ መጀመሩንም ነው የተናገሩት።፡